የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከ‹‹Derja.com›› እና ከ‹‹EthioJobs›› ጋር በመተባበር ለ2016 ዓ/ም የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተመሪዎች ‹‹Dereja Academy Accelerator Program/DAAP/ ሥልጠና ከጥር 19 - መጋቢት 22/2016 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ ማዕከሉ ሥልጠናውን በየዓመቱ እንደሚሰጥ አስታውሰው በዘንድሮው ዓመት የማዕከሉን መመዘኛዎች ያሟሉ 300 የዋናው ግቢና የጫሞ ካምፓስ የ2016 ዓ/ም ተማራቂ ተማሪዎችን ማሠልጠኑን ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው መሠረታዊ የሚባሉ ስምንት ሞጁሎችን በሁለት ወራት በገለጻና በበይነ መረብ(online) የወሰዱ ሲሆን በኢንደስትሪው ዘርፍ በተደረገ ጥናት የኢንደስትሪ ባለቤቶች ባለሙያዎች ቢኖሯቸው ባሏቸውና ምሩቃንን ለሥራ ብቁና ተፈላጊ ሊያደርጓቸው ከሚችሉ ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂና የደንበኛ አያያዝ የመሳሰሉ ሙያዊ ክሂሎቶች አንዱን በመምረጥ ለአንድ ወር ኦንላይን ሥልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት የሚያገኙ መሆኑን አስተባባሪዋ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የDereja Academy Accelerator Program /DAAP/ አሠልጣኝ መ/ር ዮሐንስ መስፍን ቀጣሪ ድርጅቶች ከአዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የሚፈልጉትን ክሂሎት እንዲያገኙ በተቀጣሪና ቀጣሪዎች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት ብሎም በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ የሥልጠናው ዓላማ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አሠልጣኙ ሥልጠናው የሦስት ወራት መርሃ ግብር ሲሆን የመጀመሪያው ሰዋዊ ክሂሎት (Soft Skil) የሚባሉ ራስን ማወቅ፣ ራስን መግለጽ፣ የተግባቦት ክሂሎት፣ የሥራ ቃለ መጠይቅን ጨምሮ በስምንት ሞጁሎች የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ሙያዊ ክሂሎት (Career Guidance) የሚባሉ በኢንደስትሪው ዘርፍ ጥናት ተደርገው ከተለዩ ሰባት የሙያ ኮርሶች አንዱን በመምረጥ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች በበይነ መረብ የሚሰጥ ነው፡፡

ሥልጠናው በራስ መተማመንን የሚፈጥር፣ ቀጣሪ ኢንደስትሪዎች ከባለሙያዎች ምን እንደሚፈልጉ ያወቁበትና ለሥራ ዓለም የሚያዘጋጅ ክሂሎት የጨበጡበት መሆኑን ሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት