አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 36 ባች 44 የድኅረ ምረቃ እና 110 የቅድመ ምረቃ በድምሩ 154 ተማሪዎች ሚያዝያ 19/2016 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎች መካከል አንዱ በሕክምና ዶክትሬት እንዲሁም 106ቱ በሜዲካል ላቦራቶሪ፣ ሜዲካል ራዲዮሎጂ፣ ኢንቫይሮሜንታል ሄልዝ እና ፋርማሲ የትምህርት መስኮች የሠለጠኑ የጤና ተማሪዎች ናቸው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የዛሬ ተመራቂዎች በዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሀገራዊ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የተከሰተውን የትምህርት ካላንደር መጓተትና ተያያዥ ችግሮች አሳልፈው ለምረቃ ቀን መብቃታቸውን አስታውሰው አብዛኛው ምሩቃን የሠለጠኑበት የሕክምናና ጤና መስክ ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደመሆኑ ማግኘት ያለባቸውን ዕውቀትና ክሂሎት በአግባቡ ወስደው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዋናነት አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልን ለተማሪዎች ሥልጠና ሲጠቀም መቆየቱን የጠቀሱት ዶ/ር ዓለማየሁ በቅርብ ወራት የራሱን ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሺያላይዝድ ሆስፒታል ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ኤባ ሚጀና ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ በግለሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ጤና መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ምሩቃን ከዩኒቨርሲቲው ያገኛችሁትን ዕውቀት፣ ክሂሎትና ልምድ በአግባቡ በመጠቀም ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀት ይገባችኋል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን(አሉምኒ) ማኅበር ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ባይነሳኝ ለምሩቃን፣ ለቤተሰቦችና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክትና ምሩቃን ቀጣይ ዘመናቸው ብሩህ እንዲሆን መልካም ምኞቷን ገልጻ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ማኅበር አባል እንዲሆኑ ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ የሬጂስትራርና አሉምኒ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ የምሩቃንን መረጃ ያቀረቡ ሲሆን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከየትምህርት ክፍሎቻቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡና ከሴት ተማሪዎች አብላጫ ውጤት ያላቸውን ምሩቃን ሸልሟል፡፡ ከአጠቃላይ ምሩቃን መካከል 3.97 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተመራቂ ኤልሻዳይ አበባው ከሜዲካል ላቦራቶሪ ት/ክፍል የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም ከሴት ምሩቃን መካከል 3.9 ያመጣችው ተመራቂ ሰላም ባይለየኝ ከሜዲካል ራዲዮሎጂ ት/ክፍል ልዩ ሽልማት ከዩኒቨርሲቲው ተበርክቶላቸዋል፡፡

በሌላ በኩል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የዕለቱ ልዩ ተጋባዥ እንግዳ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ከተመራቂዎቹ መካከል ወላጆቻቸው በመርሃ ግብሩ ላልተገኙና ድጋፍ ለሚሹ አምስት ተመራቂ ተማሪዎች ለመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች በራሳቸውና በመ/ቤታቸው ስም ሃምሳ ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት