የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማት ማበልጸጊያ ማዕከል የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ላሸነፉ ተማሪዎች ሽልማት እና በዕውቅ የሥራ ፈጠራ አማካሪና ደራሲ ቁልፍ መልእክት የማስተላለፍ መርሃ ግብር ሚያዝያ 17/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም የሥራ ፈጠራ ዕድል እየተስፋፋ በመምጣቱ ኢኮኖሚው የመነቃቃት ሁኔታ እያሳየ መሆኑን ገልጸው በዩኒቨርሲቲውም ማዕከሉ በመቋቋሙ ሥልጠናዎችን በመስጠት አሸናፊ ሃሳብ የሚያፈልቁ ተማሪዎችን ማፍራት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚደረገው ውድድር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ሃሳብ ይዞ ለመቅረብ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ዶ/ር ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ከግለሰብ ባለፈ ለተቋማት አስፈላጊ የሆነውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማስፋፋት ማዕከሉ በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አትራፊ ለመሆን በሥራ ፈጠራ ውስጥ መቃኘትና በጽናት መሥራት የሚጠበቅ ሲሆን የሥራ ፈጠራ ሃሳቦችን በየጊዜው መከለስና ማዳበር ተገቢ ነው፡፡ በቀጣይም የፈጠራ ሃሳብ ባለቤት የሆኑ ተማሪዎችን ለመደገፍ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን እንደሚያደርግ ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ አማካሪና ደራሲ ዶ/ር ወሮታው በዛብህ ባስተላለፉት ቁልፍ መልእክት ለስኬታማ ሕይወት ራስን ማወቅ፣ ለህሊና መታመን፣ ራስን ፈልጎ በማግኘት ትክክለኛ ቦታ ላይ መገኘት እና እይታን ማስተካከል መቅደም ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የበለጸጉ ሀገራት እንዲሁም የውጭና የሀገር ውስጥ ዕውቅ ባለሀብቶች የስኬታማነት መሠረታቸው ሥራ ፈጠራ ነው ያሉት ዶ/ር ወሮታው ሀገራችን አስተማማኝ ሰላሟ እንዲረጋገጥ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎችን ማፍራትና ራስ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ያለንን ዕውቀትና ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ የሥራ ፈጠራ ውድድር በየዓመቱ እንደሚካሄድ ጠቁመው ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት ከማግኘት ባለፈ የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ መሬት እንዲያወርዱ የተለያዩ ተቋማት ጋር የሚያገናኛቸው ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ተወዳዳሪዎች ከሽልማቱ ባሻገር ከዳኞች የሚሰጠውን ሃሳብ እንደ ግብዓት በመጠቀም በቀጣይ በሚኖሩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ብቁ ሆነው መገኘትና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንዳለባቸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ሳውላ ካምፓስን ጨምሮ 10 የፈጠራ ሃሳቦች ቀርበው ከ1-5 ለወጡ ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማትና የምስክር ወረቀት እንዲሁም እስከ 10 ለወጡት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች መካከል ዘመናዊ ጡብ ማምረት፣ የሻማ ሥራ፣ ‹‹Vertical Farming››፣ ‹‹Plastic Recycling Machine›› እና ‹‹All in one Ticketing Platform›› የሚጠቀሱ ሲሆን አንደኛነትን ያገኘው የሲሚንቶ ብሎኬትን የሚተካ ከአፈር የሚመረት ዘመናዊ ጡብ በሜካኒካል ምኅንድስና የ5ኛ ዓመት ተማሪ ሱሌይማን አበበ የቀረበ ነው፡፡ ተማሪ ሱሌይማን በውድድሩ ባገኘው ደረጃ መደሰቱን ገልጾ ተመራቂ ተማሪ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ሥራ በመሰማራት ስኬታማ ለመሆን መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

በውድድሩ የሁለተኛነት ደረጃን ያገኘችው የጫሞ ካምፓስ አዲስ ገቢ ተማሪ እሌኒ በዛብህ አዲስ ፈጠራ የታከለበት የሻማ ማምረት ሥራ ላይ የፈጠራ ሃሳብ ያቀረበች ሲሆን በውድድሩ በርካታ ጠቃሚ ሃሳቦችን ማግኘት እንደቻለችና ለሥራው ተነሳሽነት የፈጠረላት መሆኑን ገልጻለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት