የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የአመራርነት እና የአስተዳደር ክሂሎት ሥልጠና ሚያዝያ 22/2016 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህለ እንደገለጹት በተቋም ደረጃ በአብዛኛው አመራር ሆነው ያሉት ወንዶች በመሆናቸው ሴቶችም ወደ አመራርነት እንዴት መምጣት እንደሚችሉ ግንዛቤ ለመፍጠርና አቅም ለማጎልበት የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማለፍ ወሳኝ ምላሾችን መስጠት የሚችሉበትን አቅም እንዲያጎለብቱ፣ በሥራቸው ላይ ኃላፊነትን እንዲወስዱና ከፍ ያለ ጥረት በማድረግ የሥራ ጉዟቸውን ውጤታማ እንዲያደርጉ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ዳይሬክተሯ አመላክተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህርና አሠልጣኝ መ/ር  አቤል ሲሳይ እንደገለጹት ሥልጠናው በዋናነት ስለአመራርነትና ስለአስተዳደር ክሂሎት ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ሲሆን በተለይ ተቋማዊ አመራር በሠራተኞች መካከል የጋራ የሆነ እምነት እንዲዳብርና ራዕይን እውን ለማድረግ የሚያስችል የተግባቦት፣ የሥራና የአመራርነት ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡ በተጨማሪም አንድ ተቋማዊ አመራር ተቋሙንና ሠራተኞችን ከለውጡ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣሙ የማድረግና የተቋሙ የወደ ፊት ሥዕል ምን እንደሚመስል ግምት ውስጥ በማስገባት ሠራተኞችን ከተቋሙ ራዕይ ጋር የማስተሳሰርና ራዕዩ እውን እንዲሆን ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ እንደ አሠልጣኙ ሥልጠናው በዋናነት ሴትን እንዴት ወደ አመራርነት ደረጃ ማምጣት እንደሚቻልና ቀደም ሲል በሀገራችን ሴቶች አመራር መሆን አይችሉም የሚለውን ዕሳቤ በመቀየር በዩኒቨርሲቲው ያሉ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማበረታታትና በምን ዓይነት የአመራርነት ደረጃ ላይ እንደሉ ራሳቸውን እንዲያዩበት የተዘጋጀ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መ/ርትና አሠልጣኝ መሠረት አሰፋ እንደገለጹት አመራርነት አንድ የጋራ ዓላማን ለማሳካት በሰዎች ባህርይ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ጥበብ ሲሆን መሪውም ሆነ ተከታዮች በውስጣቸው አንድ ሊያከናውኑት የሚፈልጉትን የጋራ ግብ የያዘ ነው፡፡ ሥልጠናው በዋናነት የተዘጋጀው ሴት አመራሮች በአካባቢ፣ በቤተሰብና በሥራ ቦታ ላይ የሚደርሰውን በርካታ ጫና አልፈው ለአመራርነት ደረጃ እንዲደርሱ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሠልጣኞችም በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው መደሰታቸውን ገልጸው ኢትዮጵያን እንዴት መቀየር እንደሚቻል፣ ጊዜና አቅምን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ እንዲሁም ለቀጣይ ትውልድ የሴቶችን ተሳትፎ በጉልህ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውና ሴቶች አመራር መሆን እንደሚችሉ ማሳያ በርካታ የግንዛቤ ትምህርት እንዳገኙና ግለ ግምገማ ለማድረግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው “አመራርነት ምንድን ነው?”፣ “ሴቶችን እንዴት ወደ አመራርነት ደረጃ ማምጣት ይቻላል?” እንዲሁም ሴቶች ወደ አመራርነት ከመጡም በኋላ እንዴት ብቁ እንደሚሆኑ፣ የአመራርነት መስፈርቶች፣ ራስን መምራት፣ ቡድን መምራት፣ ተቋምን መምራት እና መሪነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚሉ ርዕሶች በስፋት የተዳሰሱበት ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት