የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝኃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ተመራማሪዎች ከእምቦጭ አረም የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሥራት አረሙ በውኃ አካላት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በሀገራችን በርካታ ሐይቆችና የውኃ አካላት ላይ እምቦጭ አረም ትልቅ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቅሰው ዓባያና ጫሞ ሐይቆችም የዚህ መጤ አረም ተጠቂ በመሆናቸው አረሙን ለማጥፋት የዩኒቨርሲቲው የብዝኃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል የተለያዩ ምርምሮችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ተ/ፕ በኃይሉ ዩኒቨርሲቲው ከኢንዶኔዥያና ከኔዜርላንድስ ባገኘው ተሞክሮ መነሻነት ለሁለት ዓመታት ምርምር ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በምርምሩም እምቦጭን በሁለት መልኩ መጠቀም እንደሚቻል ተለይቷል፡፡ የመጀመሪያው እምቦጭ አረምን ከተለያዩ ዕፅዋት ጋር በማደባለቅ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ መሥራት ሲሆን ይህም በበቆሎ ማሳ ላይ ሙከራ ተደርጎ ጥሩ ውጤት ማስገኘቱን እንዲሁም ሌላኛው የምርምር ውጤት እንቦጭን ለተለያዩ ጌጣጌጦች መሥሪያነት የሚያውል መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ ተ/ፕ በኃይሉ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት እና ከዞኑና ከከተማው የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ጋር በመተባበር ሥራ አጥ ወጣቶችን በማሠልጠን፣ በማደራጀት፣ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግና የገበያ ሁኔታ በማመቻቸት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝኃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሽቴ ጋተው በበኩላቸው ማዕከሉ ከሚያካሂዳቸው ምርምሮች አንዱ በእምቦጭ አረም ላይ መሆኑን ተናግረው አረሙን ጥቅም ላይ በማዋል ሐይቆቹን ለመታደግ የተደረጉት ምርምሮች አበረታች ውጤት ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ የእንቦጭ አረም ግንዱ በጣም ጠንካራና ከእንሰት ምርት ከምናገኘው ቃጫ ያልተናነሰ ሲሆን ከአረሙ ዘንቢሎች፣ ምንጣፎች፣ ጫማዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችና ጌጣጌጦችን መሥራት ተችሏል፡፡ በቀጣይም በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሥልጠና በመስጠት የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ለማድረግ እንዲሁም የሐይቁን ብዝኃ ሕይወት ለመታደግ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ የእምቦጭና ፓርቲኒዬም አረሞች ዋና ተመራማሪ መ/ር አታላይ አዘነ አረሞቹን በመጠቀም የተሠራው የአፈር ማዳበሪያ በበቆሎ ሰብል ላይ ተሞክሮ ጥሩ ውጤት ማስገኘቱንና በምርት ጣዕም የተሻለ ስለመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጥሩ ግብረ መልስ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ተሞክሮውን በማጠናከር አካባቢን ጽዱና አረንጓዴ ማድረግ የሚችሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን፣ የችግኝ ማፍያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት