የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ያቋቋመውን የሥዕል ስቱዲዮ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች በተገኙበት ግንቦት 5/2016 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ የአካባቢውን ባህልና ሥነ ጥበብ ማበልጸግ መሆኑን ጠቅሰው ስቱዲዮው በደቡባዊ ኢትዮጵያ ያለውን የሥዕል ዕውቀት በማበልጸግ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ እንደ ተቋም በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በአርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም የሥዕል ዝንባሌ ላላቸው የተቋሙ ሠራተኞችና ለታራሚዎች ለአንድ ዓመት የቆየ ሥልጠና መስጠታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ለሕፃናት፣ ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሥዕል ሥራ ላይ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ዕቅድ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡ የሥዕል ስቱዲዮው ለአገልግሎት ክፍት በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ መምህራን እና ተማሪዎች መጥተው እንዲጎበኙና የፈለጉትን የሥዕል ሥራዎች እንዲገዙ እንዲሁም የሥዕል ተሰጥኦ ያላቸው ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ዳይሬክተሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ባለሙያና ተመራማሪ ተመስገን ማስተዋል ሥነ ጥበብ ከሰው ልጅ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው አንዱ የባህል መገለጫ በመሆኑ ሁሉም ሰው ሥዕል የማየት ልምዱን ሊያዳብር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የሥዕል ሥራ ታሪክና ማንነታችን የሚገለጽበት ትልቅ ሀብት ነው ያሉት ባለሙያው በተገቢው መንገድ አደራጅቶና አሳድጎ መጠቀም የገቢ ምንጭ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን ከማሳደግ አንጻርም ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በሥዕል ስቱዲዮው የኢትዮጵያን ባህል፣ የተለያዩ የመሬት አቀማመጦች እና የጋሞ የእርቅ ሥርዓትን የሚገልጹ ሥዕሎችና ቅርፃቅርፆች ለእይታና ለሽያጭ መቅረባቸውን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ሥራው የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ መሆኑን ተናግረው የሥዕል ሥራውን ለማሳደግ ለዘርፉ ቅርበት ካላቸው ትምህርት ክፍሎች ጋር በማቆራኘት ለማሠራት እና አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት