የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ከጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከዞኑ በተመረጡ 10 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለመተግበር ያቀደው ‹‹የሳይንስ ቤተ ሙከራዎች አያያዝ ሥርዓት መተግበርና መልሶ ማደራጀት›› መርሃ ግብር በምዕራብ ዓባያ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከግንቦት 16-17/2016 ዓ/ም ተከናውኗል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ እንደገለጹት በሳይንስ ዘርፍ የመማር ማስተማሩን ለማቅናትና የትምህርት ጥራት ስብራትን ለመጠገን የሳይንስ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ያሉ ኬሚካሎችንና ቁሳቁሶችን መለየት፣ መልሶ ማደራጀት፣ አስተማማኝ ማድረግ እንዲሁም ጽንሰ ሃሳብን ወደ ተግባር በመቀየር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከራሳችን ቤተ ሙከራዎች በመጀመር ብክነቶችን በመቀነስና ቤተ ሙከራዎችን እንደገና በማቋቋም ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡ ሂደቱ እርስ በእርስ መማማር፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ማወቅ እና መጠቀም መቻልን እንደሚያጎለብት ዲኑ ተናግረዋል፡፡

በኮሌጁ የኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ፍሬው ደነቀ በምዕራብ አባያ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከ180 በላይ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ኬሚካሎች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው የኬሚካሎቹን ናሙና ወደ ዩኒቨርሲቲ በማምጣት በተደረገው ምርመራ ኬሚካሎቹ አገልግሎት ላይ መዋል የሚችሉ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን በብልሽት ምክንያት የተቀመጡ አምስት ማይክሮስኮፖች፣ አውቶፕሌን እና በፊዚክስና በኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ ውስጥ የነበሩ የመገልገያ መሣሪያዎች የተወሰነ ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

በኮሌጁ የፊዚክስ ት/ክፍል መምህር፣ አሠልጣኝና የፕሮጀክቱ አባል ዋስይሁን ጫማ ለቤተ ሙከራ ባለሙያ መምህራን በሴፍቲ ማኔጅመንትና የቤተ ሙከራ ዕቃዎች አጠቃቀም ዙሪያ የፅንሰ ሃሳብና የተግባር ሥልጠና የሰጡ ሲሆን አሠልጣኝ አሳዬ ካሳዬ የኬሚካሎችን የአገልግሎት ማብቂያ ቀኖች ማወቅ፣ ባህሪያቸውን መለየት፣ ሕጎችን መጠቀም እና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ላይ አሠልጥነዋል፡፡

የምዕራብ ዓባያ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ዋና ርእሰ መምህር አቶ በርገኔ ባፋ እንደተናገሩት በሦስቱም ቤተ ሙከራዎች ላይ በተደረገው መልሶ የማደራጀት ሥራ ኬሚካሎችን መለየት እንዲሁም ለፊዚክስ፣ ለባዮሎጂና ለኬሚስትሪ መምህራን ሥልጠና መስጠት የተቻለ ሲሆን የቤተ ሙከራ ኬሚካሎችን አስመልክቶ ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡

በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያና የአኒሜሽን ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ታደለች ቶላ በበኩላቸው በባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪና ፊዚክስ ቤተ ሙከራዎች ላይ የሚሠሩ መምህራንንና ተማሪዎችን ማሳተፍ የትምህርት ስብራቱን ለመጠገንና ስኬታማ የቤተ ሙከራ ሥራዎችን በማከናወን ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያደርጋል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት