የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አዲስ በሚከፈተው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሚያገለግሉ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን እና በአምስቱ ካምፓሶች ለሚገኙ የተማሪዎች አገልግሎት ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎች በኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር (Infection Preventing and Controlling) ዙሪያ ከግንቦት 13-24/2016 ዓ/ም በሁለት ዙሮች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አሠልጣኝ ኃይለገብርኤል አቦምሳ ሠልጣኞች አዲስ በሚከፈተው ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ከመጀመራቸው በፊት ስለ ኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊውን ዕውቀት እንዲጨብጡ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ኃይለገብርኤል ሥልጠናው በእጅ ንጽሕና መጠበቅና ቴክኒኮች፣ የእጅ ንጽሕና ባለመጠበቅ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች፣ ሆስፒታል ውስጥ ሊሰራጭ የሚችልን ኢንፌክሽን መከላከል፣ የሆስፒታል ጽዳት አገልግሎት አጠባበቅ፣ ከሆስፒታል የሚወጣ አካባቢን ሊበክል የሚችል ቆሻሻ አወጋገድ፣ የኢንፌክሽን መተላለፊያ መንገዶች፣ ለሕክምና አገልግሎት የምንጠቀማቸውን መሣሪያዎች ማጽዳት እንዲሁም መድኃኒት የተላመዱ ተዋስያንን ስርጨት መግታት የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎች ግንዛቤ አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው፡፡

በጤና ሚኒስቴር ‹‹Health System Innovation and Quality Lead Executive Office›› የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም አማካሪ አሠልጣኝ ካሡ ጦላ በበኩላቸው በጤና ድርጅቶች ውስጥ የተለያዩ ተህዋስያን(Microorganisms) የመተላለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ የጤና ባለሙያዎች ለሕመምተኛው አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ትልቅ የጤና ተቋም እንደ መሆኑ ተላላፊ የሆኑና ያልሆኑ ሕመሞችን ለመታከም በርካታ ተገልጋዮች የሚመጡ በመሆኑ ኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠርን በሁሉም ሥራ ክፍል ሁሌም ሳይዘናጉ መተግበር እንደሚገባ አሠልጣኙ አሳስበዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ እንደገለጹት ኢንፌክሽንን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ሥልጠና መስጠት ለሁሉም ጤና ተቋማት መሠረታዊ ሲሆን አዲስ በሚከፈተው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገቡ ባለሙያዎች ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና በመደጋገፍ ተቋሙን ለመገንባት ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ክሊኒክ የጤና ባለሙያና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ አንዱዓለም ሳሙኤል ሥልጠናው ለሁሉም የዩኒቨርሲቲው ጤና ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም በባለቤትነት አብሮ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ዕውቀት ማግኘታቸውንና በዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት እንዲሁም ሥልጠናውን በተግባር ሠርቶ ለማሳየት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ለሠልጣኞች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት