በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ት/ት ክፍል "Improving the Quality of English Language Teaching Through Reflection " በሚል ርእስ በጋሞ ዞን በሚገኙ አራት 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚሠራ 1.75 ሚሊየን ብር የተመደበለት ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ኅዳር 21/2017 ዓ/ም ይፋ ተደርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ በከምባ ፣ ጨንቻ ፣ ምዕራብ ዓባያና ሰላምበር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ፀጋብርሃን ወዳጅ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅርፍ የሚያስችሉ መንገዶችን በማመላከት ረገድ ጉልህ ሚና ሊጫወት አንደሚችል ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱ ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ ለፕሮጀከቱ ማስፈጸሚያ ከፍተኛ በጀት የመደበ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፀጋብርሃን ዩኒቨርሲቲው ለሥራው የሰጠውን ትኩረት ከግምት በማስገባት በምርምር ፕሮጀክቱ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ለሥራው ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ኤርሚያስ በፍቃዱ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ሥራዎች ባሻገር ማኅበረሰቡን በተለያዩ መንገዶች የሚጠቅሙ ችግር ፍቺ ምርምሮችንና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በኮሌጁ ከተሰሩና እየተሰሩ ከሚገኙ የምርምር ፕሮጀክቶች መካከል የትምህርት ጥራት መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ይገኙበታል ያሉት አቶ ኤርሚያስ ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም በትምህርት ጥራት ላይ አተኩረን እየሰራን ስለመሆናችን ማሳያ ነው ብለዋል።
የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የምርምር ፕሮጀከቱ ዋና ተመራማሪ ማንጉዳይ መርጮ (ዶ/ር) በሀገሪቱ በሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በተለያዩ ምክንያቶች በአግባቡ እና በበቂ ሁኔታ እየተሰጠ አለመሆኑ የምርምር ፕሮጀክቱን ለመስራት ያነሳሳ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል። መምህራን በየዕለቱ የሚሰሩትን ሥራ በራሳቸው ገምግመው ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን በመለየትና በግል ግምገማቸው ላይ ተመሥርተው ማስተካከያ የማድረግ ልማድ የላቸውም ያሉት ዶ/ር ማንጉዳይ መምህራን የራስን የትምህርት አሰጣጥ በየዕለቱ በመገምገም የተሻለ ትምህርት ለተማሪዎች ማቅርብ እንዲችሉ በዚህም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ ጥራትን ማሻሻል የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማና ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመታት የሚቆይና ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የትግበራ ደረጃዎችን የሚያልፍ ሲሆን በዚህም የፕሮጀክቱ ምዕራፍ መምህራን ራሳቸውን ከማየትና ከመገምገም አንጻር ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሥልጠና አንደሚሰጣቸው ዶ/ር ማንጉዳይ ጠቁመዋል። በዚህ የምርምር ፕሮጀክት የሚገኙ ውጤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ መ/ራን ቋንቋውን በተሻለ መንገድ እንዲያስተምሩ የሚያስችሉ ዕድሎችን የሚፈጥርና ለፖሊሲ አውጪዎችም ሆነ ለትምህርቱ ማስተማሪያ የሚውሉ የተለያዩ ግብአቶችን ለሚያዘጋጁ አካላት የፖሊሲም ሆነ የአሠራር ለውጥ ሊያምጡ የሚችሉ እንዲሁም ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚረዱ ውጤቶች ከፕሮጀክቱ በዋናነት ይጠበቃል ብለዋል። ከዚህም ባሻገር ከምርምር ፕሮጀከቱ የሚገኙ ውጤቶችን እንዲሁም አዳዲስ ግኝቶችን በተለያዩ አማራጮች በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተደራሽ ለማድረግ ስልት መነደፉንም ዶ/ር ማንጉዳይ አውስተዋል።
የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብረሃም አምሳሉ በመዝጊያ ንግግራቸው በትምህርት ዘርፍ እንደ ሀገር ከገጠመን ስብራት ለመውጣት በመሰል ምርምሮች ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ዘርፍ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት በእጅጉ የሚበረታቱ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ዩኒቨርሲቲው በመስኩ የጀመራቸውን የተለያዩ ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አሁን ላይ የተጀመረው ፕሮጀክትም ለዘርፉ መሻሻል የሚጠቅም በመሆኑ ለሥራው ስኬት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የአራቱም ወረዳዎች ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና መምህራን፣ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አባላትና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት