በግጭት ምክንያት የገዛ መኖሪያ ቤታቸው ፈርሶ ለወራት በሽራና በፕላስቲክ መጠለያዎች ውስጥ በከባድ እንግልት ሲኖሩ የነበሩ 100 አባወራዎች፣ ከዓመታት ጨለማ በኋላ አዲስ የብርሃንና የተስፋ ምዕራፍ ጀምረዋል። ትናንት መስከረም 30/2019 ዓ/ም በኮንሶ ዞን ገላቦ ቀበሌ በተካሄደ ደማቅ የምረቃና የርክክብ ሥነ-ሥርዓት፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በዓለም አቀፍ አጋሮቹ የተገነቡት 100 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ከሶላር ኤሌክትሪክ መብራት ዝርጋታ ጋር ለተፈናቃይ ቤተሰቦቹ በይፋ ተላላፈዋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ይህ ግዙፍ የሰብአዊና የማህበረሰብ ድጋፍ ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ቤት አስተባባሪነት እና በኦክስፎርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ የአደጋና ልማት ማዕከል (CENDEP) ትብብር የተከናወነ ሲሆን፤ ሙሉ የገንዘብ ድጋፉ በጀርመኑ ጌርዳ ሄንከል ፋውንዴሽን (Gerda Henkel Foundation) የተሸፈነ ነው።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር መኖሪያ ቤት ከመሠረታዊ መጠለያነት የዘለለ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል። "ቤት የመኖር፣ የሰው ልጅ ክብር ማሳያ፣ የደህንነት፣ የሰላምና የነፃነት ማረፊያ እንዲሁም የቤተሰብና የትውልድ መሠረት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም፣ መጠለያው በተለይም እናቶችንና ሕፃናትን ከጥቃትና ከከባድ አደጋዎች በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ ሕፃናት በሰላም አድገው፣ በትምህርታቸው ላይ አተኩረው የሚማሩበትና የተሻለ የወደፊት ሕይወት የሚገነቡበት አዲስ ተስፋ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር እና ከምርምር ዋና ዋና ተልእኮዎቹ ባሻገር በተለይም በንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በታዳሽ ኃይል ዝርጋታ፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በግብርናው ዘርፍ፣ በትምህርት ጥራትና ማስፋፋት እንዲሁም ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ፕሮጀክቱ ሦስት ሀገራትን (ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ኢትዮጵያን) ያስተሰረረ መሆኑን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው በሆነ መልኩ በአንድ ፕሮጀክት ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ማለትም የቤት ግንባታን እና የሶላር ኃይል ዝርጋታን በአንድ ላይ የያዘ በመሆኑ ፕሮጀክቱን እጅግ ልዩ እንደሚያደርገው አብራርተዋል። አክለውም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚደረጉ አጋርነቶች እንዲህ ያሉ ዘላቂ ፍሬዎችን እያፈሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የፕሮጀክቱ እውን መሆን የአካዳሚክ ተቋማት ለማህበረሰብ ችግር መፍትሔ የመስጠት አቅም ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር ተክሉ አያይዘውም ይህ እጅግ አስፈላጊና አበረታች ፕሮጀክት ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ከግቡ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ላደረጉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ ለለጋስ ድርጅቶች፣ ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ለሕግ ትምህርት ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካላትና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የጌርዳ ሄንከል ፋውንዴሽን የቦርድ አባልና የቀድሞው የጀርመን አምባሳደር ክቡር ማርቲን ኮብለር በፕሮጀክቱ አስደናቂ ዕድገትና ውጤት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታና መደነቅ ገልጸዋል። አምባሳደሩ እንዲህ ያሉ ሩቅ እና ለመድረስ አስቸጋሪ መንገዶች ባሉባቸው አካባቢዎች እንዲህ ያለ ግዙፍና ጥራት ያለው ሥራ መከናወኑ እንደሚያኮራ ተናግረዋል። በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትና ግለሰቦች ሁሉ በሙሉ ልብ አመስግነው፤ ፋውንዴሽኑ በቀጣይነትም እንደዚህ ያሉ በምርምር ላይ የተመሰረቱ የልማት ፕሮጀክቶችን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በመጨረሻም ወላጆች ህፃናት ልጆቻቸውን በትምህርት እንዲያንጹና እንዲያስተምሩ አፅንኦት ሰጥተው መክረዋል።
የኮንሶ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ እንደገለጹት ይህ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የጭቃና የእንጨት ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በግጭቱ ምክንያት የተሸረሸረውን የሕዝቦቻችንን ሰብአዊ ክብር ያስመለሰ፣ የተፈናቃዮችን ተስፋ ያለመመ፣ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በኮንሶ ሕዝብ መካከል ያለውን አብሮነትና ፍቅር የበለጠ ያጠናከረ ታላቅ ተግባር ነው።
የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አብርሃም ክንፈ ስለ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሂደት፣ የትግበራ ደረጃዎችና እስከ አሁን ከተከናወኑት ተግባራት ጋር ተያይዞ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ትምህርት ቤቱ በኮንሶ ዞንና በተለያዩ አካባቢዎች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ያከናወናቸውን አበራች ሥራዎች ያነሱ ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት በትምህርት ቤቱ አስተባባሪነት የተከናወነ ትልቅና ልዩ ታሪካዊ ተግባር በመሆኑ የተሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል።
የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ያሊሾ ግርማ ስለ ሶላር ፕሮጀክቱ በሰጡት ማብራሪያ የሶላር ፕሮጀክቱ በሦስት የተለያዩ ቦታዎች በክላስተር የተገጠሙ ሦስት የሶላር ፓነሎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል። እያንዳንዱ ፓነል 1,000 ዋት ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 3,000 ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው። ይህ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ለአዲሶቹ 100 የመኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሪክ የሚያቀርብ መሆኑንም አብራርተዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት፣ ውጤታማ ትግበራና ከግብ መድረስ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት፣ ለለጋስ ድርጅቶች፣ ለዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ የከፍተኛ እውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።
ከነበሩበት የፕላስቲክና የሽራ መጠለያ አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው የቋሚ ቤትና የሶላር ኤሌክትሪክ ብርሃን ባለቤት የሆኑት የተፈናቃይ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ታላቅ ደስታና እርካታ በመግለጽ፣ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ለአጋር ድርጅቶች ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

