አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 10ኛውን የማኅበረሰብ ጉድኝት ቀን ‹‹በተፈጠረው እድል ማኀበረሰባችንን እናገልግል›› በሚል መሪ ቃል ኀዳር 26/2018 ዓ/ም በተለያዩ መርሐ ግብሮች በዋናው ግቢ በድምቀት አክብሯል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በትምህርት ሚኒስቴር የማኀበረሰብ ጉድኝት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰራዊት  ሃንዲሶ የትምህርት ተቋማትን  የማኀበረሰብ ጉድኝት አሠራር ለማሻሻል በርካታ የሪፎርም አጀንዳዎችን በመቅረጽ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባር የተሳትፎ ጉዳይና የበጎ አድራጎት ሥራ አለመሆኑንና ይልቁንም በጋራ ምን ማሳካት ይቻላል የሚል የፍልስፍናና ስትራቴጂ ለውጥ የሚሻ እይታ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የጉድኝት ሥራ የመማር ማስተማር ዋና አንጓና በትምህርት ተገቢነትና ጥራት ቀልፍ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ትልቅ ታሪክ ያለው መሆኑንና ቀጣይ መሠረታዊ የማኀበረሰብ ጉድኝት ፍልስፍናና ስትራቴጂያዊ ለውጦች ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት እንዳለበት መሪ ሥራ አስፈጻሚው አሳስበዋል፡፡

የእለቱ ክብር እንግዳ የሆኑት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል ዶ/ር ደምሴ አድማሱ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ የተለያዩ የሥራ ዘርፎችና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመምራት ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሁራንና ተመራማሪዎችን በማፍራት በሀገር ልማት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ  ዩኒቨርሲቲ ምርምርን መነሻ ባደረጉ ችግር ፈቺ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማኅበረሰባችንን ተጠቃሚ እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ዩኒቨርሲቲው በሥሩ በሚገኙ ኮሌጆች፣ ኢንስትቲዩቶች እና ት/ቤቶች በርካታ ማኀበረሰብ ተኮር ተግባራት ማከናወን መቻሉንና በተለይ ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ ማድረግ እና የአባያና ጫሞ ሐይቆች ሥነ ምኅዳር  ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዩኒቨርሲቲው ራእይ መሳካት በጉድኝት መሥራትና ለማኀበረሰቡ የሚሰጡ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችንና  የተሻሉ ተሞክሮዎችን ማስቀጠል ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን ፈጣን እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ምሁራንን ከማፍራት ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማኀበረሰብ ጉድኝት በኩል ተገቢውን ሚና እየተወጣና በዚህም የማኀበረሰቡን የትኩረት መስክ በመለየት የሳይንስ ሥራዎችን በማስተባበርና በመምራት፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶችና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሸጋገሩና እንዲለሙ እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በማሳደግ በኩል በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብዛትና ጥራት ያላቸው ማዕድናት ባለቤት መሆኑ በጥናትና ምርምር መረጋገጡንና ዩኒቨርሲቲው ለኢንደስትሪው የሚሰጠውን የማማከር አገልግሎት በማሳደግ በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሠራ ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል። 

የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በዩኒቨርሲቲው በርካታ የማኅበረሰብ  ክፍሎችን ችግር የፈቱ፣ አኗኗር ያሻሻሉ እና የተቋማትን አሠራር ያዘመኑ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ፣ በነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ በታዳሽ ኃይል አቅርቦት፣ በነፃ የጤናና ሕክምና አገልግሎት እንዲሁም የትምህርት ስብራትን ከመጠገን አንጻር የተቃኙ በርካታ ተግባራት ያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ዩኒቨርሲቲው ባከናወናቸው የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ተጠቃሚ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮችና የተቋማት ኃላፊዎች ምስክርት የሰጡ ሲሆን በመስኩ በተመዘገቡ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጌጥ፣ የሁሉም ጓዳ፣ እንደ አባያና ጫሞ ሐይቆች የአርባ ምንጭ ከተማ ውበትና ሞገስ የሆነ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍም በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ አንጋፋ ተቋም መሆኑን አንስተዋል። እንደ ዲንጋሞ ፒኮ ሃይድሮ ፓወር ያሉ ማኅበረሰብን ከጨለማ ያወጣ ዓይን ከፋች ፕሮጀክት ሠርቶ ያሳየ ዩኒቨርሲቲ አካል መሆን ያኮራል ያሉት ተሳታፊዎቹ በቀጣይም ዩነቨርሲቲው መሰል ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን መሥራቱን በስፋት አጠናክሮ እንዲቀጥል መክረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት