በየዓመቱ የምርምር ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ጉባኤ የሚያዘጋጀው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 12ኛውን ዓመታዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ ወርክሾፕ ጥር 23/2017 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ኢንስቲትዮቶች፣ ኮሌጆች፣ ት/ቤቶችና የምርምር ማእከላት እየተከናወኑ ያሉ ምርምሮች የደረሱበትን ደረጃ ለመፈተሽ ብሎም ተግዳሮቶችን ለይቶ መፍትሔ ለመስጠት ወርክሾፑ መዘጋጀቱን የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተወካይና የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ጠቁመዋል፡፡ መድረኩ ተመራማሪዎችን የሚያቀራርብ፣ ዕውቀትና ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ ዕድል የሚሰጥ እንዲሁም በርካታ የምርምር ሃሳቦች የሚገኙበት ነውም ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎች እንቅስቃሴና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ባቀረቡት ገለጻ እንደተመለከተው በዩኒቨርሲው ስምንት የምርምር ማእከላትና ዘጠኝ የምርምር ማስተባበሪያ ቢሮዎች ያሉ ሲሆን በክንውን ላይ ከሚገኙ 551 ምርምሮች 334ቱ በዚህ ዓመት ተጠናቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉ/ም/ ፕሬዝደንት ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በመስክ ልየታ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንደመመረጡ ምርምር የተወሰኑ ሰዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባራችን ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም መሰል መድረኮች ጅምር ሥራዎቻችንን በሰፊው ለማስቀጠልና ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ወርክሾፑ እያንዳንዱ ፋከልቲና ት/ክፍል በሥሩ የሚሠሩትን ምርምሮች በመገምገም ያሉ ክፍተቶችንና ቀጣይ አቅታጫዎችን የሚለይበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወርክሾፑ የመክፈቻ መርሃ ግብር የዲንጋሞ መለስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ማኅበረሰብ አቀፍ የቆዳ ሌሽማኒያሲስ/ቁንጭር/ ሕክምና በኦቾሎ አካባቢ እና የአባያ ሐይቅ ዳርቻና ደሴቶች ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ታሪክን አስመልክቶ የተሠሩ ምርምሮች በጋራ መድረክ የቀረቡ ሲሆን ሌሎች የምርምር ሥራዎች በየኮሌጁና ኢንስቲትዩቶቹ የሚገመገሙ ይሆናል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከክርስቲያን ኤይድ ግብረሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በካምባ ዙሪያ ወረዳ ዲንጋሞ ቀበሌ ማይጸሌ ወንዝ ላይ እያስገነባ የሚገኘው መለስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን አስመልክቶ የፕሮጀክቱ ማኔጀር ኢ/ር በየነ ፈየ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን ፕሮጀክቱ 15 ኪ.ዋ ኃይል የሚያመነጭ መሆኑን፣ በቅርቡ የኃይል ማመንጨት የተሳካ የመጀመሪያ ሙከራ መደረጉን፣ የኤሌክትሪክ ፖሎች ተከላ መከናወኑንና ቀሪ የመስመር ዝርጋታ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በጋሞ ዞን ኦቾሎ አካባቢ Cutaneous Leishmaniasis/የቆዳ ሌሽማኒያሲስ ወይም ቁንጭርን ‘Cryotherapy’ በሚባለው መንገድ ፈሳሽ ናይትኖጂንን በበሽታው በተጎዳው ቆዳ ላይ በቀጥታ በመቀባት እና ‘Miltefosine’ በተባለው የሚዋጥ መድኃኒት በማከም ውጤቶችን ለመመዝገብ የተደረገውን ጥናት አቅርበዋል፡፡ ጥናቱ ቁንጭርን በሁለቱ መንገዶች ለማከም ያለውን መልካም አጋጣሚና ችግሮች ለመለየት የረዳና ከአንድ እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ የመዳን መጠን፣ መሻሻሎች፣ የጎንዮሽ ጉዳቶችና ሌሎችም ውጤቶች የተመዘገቡበት እንዲሁም በጥናቱ ከተካተቱ ሕመምተኞች በጎ ምላሽ የተገኘበት መሆኑን ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡ የቁንጭር በሽታ መኖሩ ከተረጋገጠ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረና በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ የጤና እና የሥነ ልቦና ችግር እያስከተለ ያለ ቢሆንም ትኩረት አለማግኘቱንና በምርምር ተደግፎ መፍትሔ ያልተፈለገለት መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪው ጥናቱ በዘርፉ የመጀመሪያና ዐይን ከፋች በመሆኑ ተመራማሪዎች በሰፊው እንዲሠሩበት ጥቆማቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት