አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 12ኛውን ምርምር ለልማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም ዛሬ መጋቢት 18/2018 ዓ/ም በጫሞ ካምፓስ አካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሲምፖዚዬሙ በቂ የዕውቀትና የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ ለማኀበረሰቡ የተሻለ ተጠቃሚነት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚስተዋሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የማኀበራዊ ሳይንስ፣ የኢኮኖሚና ማኔጅመንት፣ የሥነ ትምትርትና ሥነ ባሕርይ እንዲሁም የሕግ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ትብብርና ሚና አስፈላጊ መሆኑንም ዶ/ር ተክሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተመራማሪዎችን የምርምር አቅም ለማሻሻል የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦች የሚገኙባቸው በርካታ ሀገር ዓቀፍና ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬሞችን ሲያከናውን መቆየቱንና ይህም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም ሀገር አቀፍ የምርምር የትኩረት አቅጣጫን በመከተል ማኅበረሰቡን አሳታፊና በተግባር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣ የከተሞች መስፋፋት፣ ትምህርትና ጤና እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች የወቅቱ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች መሆናቸውንና ለዚህም የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ከሀገሪቱ ፖሊሲ ጋር የሚገናኙ፣ የምርምር አቅም የሚገነቡ፣ ማኀበረሰቡን ያሳተፉ እና ዕውቀትን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችሉ ሊሆን ይገባል ብለዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባዘጋጀው ሲምፖዚዬም በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ በትምህርት ቤቱ ተመራማሪዎች ብርቱ ጥረትና ትብብር ዩኒቨርሲቲው ተደራሽ በሆነባቸው በክልሉ በሚገኙ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እንዲሁም ለፖሊሲ አውጭዎችና ለግል ተቋማት ግብአት የሆኑ በቂ የጥናትና ምርምር ሥራ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ የማኀበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ፣ የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ እንዲሁም የሕግ ትምህርት ቤት ተመራማሪዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ፣ ወላይታ፣ ጂንካና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎች እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት በሲምፖዚየሙ ተሳትፈዋል። በሲምፖዚዬሙ 24 የምርምር ሥራዎች ቀርበዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





