የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በጾታና ሥርዓተ ጾታ ምንነት፣ በሥነ ተዋልዶ ጤናና የጤና መታወክ እንዲሁም በጾታዊ ጥቃት ባሕሪያትና መሰል ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጥቅምት 9/2017 ዓ/ም ለአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤት ሴት ተማሪዎች የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ርት ገሊላ ቢረሳው እንደገለጹት ሥልጠናው ሴት ተማሪዎች በት/ቤትና ከት/ቤት ውጭ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመሻገር ጤናቸውን በመጠበቅና በተሻለ ውጤት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መቀላቀል የሚችሉበትን የሕይወት ተሞክሮ ማካፈልና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የሥነ ተዋልዶ ጤና መምህር ዶ/ር ንጉሤ ቡቴ የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግር ውስብስብና ዕድሜ ልክ ሊያሰቃይ የሚችል በመሆኑ ለሥነ ተዋልዶ ጤና ችግር እና ጾታዊ ጥቃቶች ከሚያጋልጡ ባሕሪያት በመቆጠብ ዓላማ ያለው ተማሪ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡

መ/ርት ፍሬሕይወት ኃይሌ በበኩላቸው የሰው ልጅ ጤናማ የሚባለው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጤንነቱ ሲረጋገጥ መሆኑን ተናግረው በማኅበረሰባችን ይህንን ጤናማ ሕይወት የሚያውኩ ጾታን መሠረት በማድረግ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና የተለያዩ ጫናዎች በሴቶች ላይ በስፋት የሚስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ወ/ሮ አበበች አዳነ ባስተላለፉት መልእክት ሴት ተማሪዎች አዋዋላቸውንና ጓደኛቸውን በሚገባ በመምረጥ ለነገ ዓላማቸው መሳካት አስተውለው መጓዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት