የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ከደቡብ ኦሞ፣ ከሰገን አካባቢ ህዝቦች፣ ከወላይታና ከዳውሮ ዞኖች ለተወጣጡ ከ60 በላይ የጤና ጣቢያና የሆስፒታል ባለሙያዎች የስጋ ደዌ፣ የቲቢና የኤች አይ ቪ/ኤድስ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና ከየካቲት 27 - መጋቢት 10 /2008 ዓ/ም ለአስር ቀናት በሁለት ዙር ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የሥልጠናው ዓላማ የቲቢ በሽታ ስርጭትን መከላከል፣ መድሃኒት ለተላመደ የቲቢ በሽታ የሚሰጥ ህክምና እንዲሁም የቲቢና ስጋ ደዌ ህሙማንን አፈላልጎ ህክምናውን እንዲያገኙ ማስቻልን አስመልክቶ ለሀኪሞች፣ ለቤተ-ሙከራና ለመድሃኒት ቤት ባለሙያዎች፣ ለጤና መኮንኖችና ለሚድዋይፎች ግንዛቤን ማስጨበጥ መሆኑን የኮሌጁ ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ዓለሙ ጣሚሶ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ስጋ ደዌ፣ ቲቢና ኤች አይ ቪ ኦፊሰር ሲስተር ፍቅርተ አበራ እንደገለጹት መንግስት ቲቢ፣ ኤች አይ ቪና  ስጋ ደዌን  ለመከላከል ቁርጠኛ በመሆኑ ከላይኛው እርከን ጀምሮ ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ በአንድ ለአምስት የጤና ልማት ሠራዊት አደረጃጀት ውጤታማ እንቅስቃሴ በመጀመሩ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ በማመቻቸትና ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለህሙማን መድሃኒቶች በአግባቡ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድም አመርቂ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

የቲቢ በሽታ በሳይንሳዊ አጠራር “Mycobacterium tuberculosis” ተብሎ በሚጠራ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ሲሆን በሀገራችን በተለምዶ የሳምባ ነቀርሳ እየተባለ ይጠራል፡፡ በሽታው ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ሲሆን በምግብ እጥረት፣ በካንሰርና በኤች አይ ቪ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የሰውነት መከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች የበለጠ ለበሽታው ይጋለጣሉ፡፡ በሽታው በማንኛውም የሰውነት አካል ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ የሚከሰተው በሳምባ ላይ ነው፡፡

የስጋ ደዌ በሽታ “Mycobacterium Leprae” በሚባል ባክቴሪያ የሚመጣ ሲሆን በቀጥታ በትንፋሽ አማካኝነት የሚተላለፍና ምልክቶችን ሳያሳይ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ በሽታ ነው፡፡ የበሽታው ምልክቶች ሳይታዩ መቆየት በሽታውን ለመለየት ቢያዳግትም በህመምተኛው የሰውነት ክፍሎች ላይ በግልጽ የሚታዩ ነጣ ነጣ ያሉ ምልክቶች ሲታዩ ወዲያውኑ ህክምና ማግኘት ካልተቻለ ለከፍተኛ አካል ጉዳትና የነርቭ በሽታ ያጋልጣል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ100 ሺህ ሰው መካከል በ207 ሰው ሁሉም ዓይነት የቲቢ በሽታ ይኖራል ተብሎ ይገመታል፡፡በክልል ደረጃ ቀደም ሲል የነበረውን 39,748 አሀዝ መነሻ በማድረግ በ2008 ዓ/ም 19,374 የቲቢ ህመምተኞችን ለማከም ዕቅድ ተይዞ ባለፉት ስድስት ወራት 11, 918 ህመምተኞች ህክምናውን እየተከታተሉ ሲሆን አፈፃፀሙ 62% ነው፡፡

በስልጠናው የቲቢና የስጋደዌ በሽታን በመከላከል ረገድ ወቅታዊ የህክምና አሰጣጥ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ የገለጹት ሰልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ማህበረሰቡ ለማውረድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡