በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅና በኢፌዴሪ የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጄንሲ ትብብር ‹‹ዘመናዊ የባንክ እድገት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ 9ኛው ሀገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ግንቦት 8/2008 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዓውደ ጥናቱ ዓላማ የመንግስት ፋይናንስ ተቋማት በአሰራር ሂደት መከተል ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታ እንዲሁም በዘርፉ ለሚታዩ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች በጥናት የተደገፉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማሳየት ብሎም የባንኩን ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድጉ ግብዓቶችን በማሳየት ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ መወያየት መሆኑን የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ወንድወሰን ጀረኔ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ከፌዴራልና ከክልል መሥሪያ ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠር ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማካሄድ፣ ዩኒቨርሲቲው በሀገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳየት እና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ መነቃቃትን በመፍጠር የምርምር ተሳትፎውን ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
የኢፌዴሪ የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል እንደገለጹት በሀገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ መቶ አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በ1963 ዓ/ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መቋቋም ለዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መሠረት ሆኗል፡፡ ዘርፉ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከፍተኛ ለውጥን እያሳየ ሲሆን የአገልግሎት አሰጣጡንና የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን፣ ተደራሽነቱን ለማስፋትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቀልጣፋና ተወዳዳሪ በመሆን የመንግስት የልማት ፓሊሲዎችን ለማስፈፀም በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቃል፡፡
በዓውደ ጥናቱ ከተለያዩ ተቋማት በመጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ዙሪያ የተሰሩ ዘጠኝ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን በመንግስት የፋይናስ ተቋማትም ሆነ በግል ባንኮች ላይ ያሉ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ የተለያዩ የገንዘብ ተቋማት በአንድ ሀገር መኖራቸው ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች ብቸኛ የገንዘብ ምንጭ ሆነው ኢኮኖሚውን በመደገፍ የጎላ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ይሁን አንጂ የፋይናንስ ተቋማቱና የባንኮች ቁጥር እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ በሚችሉበት ደረጃ አለመሆናቸው በጥናት አቅራቢዎቹ ተዳሷል፡፡ ከዚህ አንፃር የግል ባንኮችም ሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ሴክተሮች በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጥናቶቹ አመላክተዋል፡፡
የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ የተቋማቱን አሠራር ለማሻሻል፣ አቅማቸውን ለማጎልበትና፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እንዲሁም ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በጥናትና ምርምር ተደግፎ በጋራ እንደሚሠራ አስገንዝቧል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ተለዋዋጭነት ባለው የቢዝነስ ዓለም የፋይናንስ ተቋማት ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ ይበልጥ ውጤታማና ቀልጣፋ በመሆን የማህበረሰቡን ፍላጎት በሚጠበቀው ደረጃ ለማርካት በተግባር የተደገፉ ምርምሮች በባለሙያዎች ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከመሥራት ጎን ለጎን ከአጄንሲው ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ለዘርፉ መጎልበት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡
በዓውደ ጥናቱ የኢፌዴሪ የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፣ ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች የመጡ እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችና መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት