የግንቦት 20 ድል 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ግንቦት 18/08 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ግንቦት 20 ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን የማሽቆልቆል ምዕራፍ ተዘግቶ የእድገትና የብልጽገና እዲሁም የዲሞክራሲ ብርሃን የፈነጠቀ የአዲስ ምዕራፍ መሸጋገሪያ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ ውጤታማ በመሆን ሰማዕታት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡትን ሀገር ህዳሴዋን ማስቀጠል ይገባዋል፡፡ ለዚህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሉ ተማሪዎች በእውቀትና በሥነ-ምግባር ታንፀው ትምህርታቸውን በስኬት ለማገባደድ እንዲጥሩ አሳስበዋል፡፡
‹‹የማሽቆልቆል ምዕራፍ ተዘግቶ የእድገት ምዕራፍ የተከፈተበት የሩብ ምዕተ ዓመት የትግልና የድል ጉዞ›› በሚል ርዕስ በቀረበው የመወያያ ሰነድ እንደተመለከተው ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሀገሪቱ ለአምስት መቶ ዓመታት የተጓዘችበት የማሽቆልቆል ሂደት ተገትቶ በእድገትና ዲሞክራሲ አቅጣጫ የተጓዘችባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡
ምዕራፉ በማህበራዊ ልማት፣ በዲሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በመሠረተ ልማት፣ በብሔራዊ መግባባት እንዲሁም በከባቢያዊና ዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነት ከፍተኛ እመርታ የታየበት ነው፡፡ ይህም ለውጥ ሊመዘገብ የቻለው በዲሲፕሊንና በተግባር አንድነት የተገነባው አመራር ጠንካራ ርዕዮተ ዓለምን ይዞ ህዝቡን ማስተባባር በመቻሉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሥርዓቱ በርካታ አዎንታዊ ለውጦችን ያመጣ ቢሆንም በቀጣይ ትኩረትን የሚሹ ተግዳሮቶች መኖራቸውም በውይይት መድረኩ ተወስቷል፡፡ ከችግሮቹ ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢነት ሀገሪቱ የጀመረችውን የስኬትና የዲሞክራሲ ጉዞ በእጅጉ የሚያዳክም በመሆኑ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የተቀናጀ ትግል ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡
የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የግንቦት 20 ድልን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲሞክራሲያዊ ነፃነት መቀዳጀቱን ተናግረዋል፡፡ የተመዘገቡ ለዉጦችን ለማስቀጠል ብሎም በአንዳንድ ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በየደረጃው ያለው አመራር ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይገባዋል፡፡
በበዓሉ የዩኒቨርሲቲዉ አመራሮች፣ የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣ መምህራን እና ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን የጋሞ ጎፋ ዞን ኪነት ባንድ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀትን ቸሮታል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት