ከስፖርት አካዳሚ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት መካከል በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በነጭ ሳርና አባያ ካምፓሶች የተሠሩት ደረጃቸውን የጠበቁ ጂምናዚየሞች፣ የእግር ኳስ ሜዳዎችና ኦሎምፒክ ስታንዳርድ የዉሃ ዋና ገንዳ ለግቢውና ለአካባቢው ስፖርት አፍቃሪ ማህበረሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ማዕከላቱ ክልላዊና ሀገራዊ ውድድሮችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ለማካሄድ የሚያስችሉ ዘመናዊ የስፖርት መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች የተሟሉላቸው እና በርካታ ተገልጋይ የማስተናገድ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡
የአካዳሚው ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው እንደገለፁት አካዳሚው ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ በሁለቱም ጾታዎች በርካታ ታዳጊ ህጻናትን በእግር ኳስ ፕሮጀክት በማቀፍ እያሰለጠነ ይገኛል፡፡ በ2008 ዓ/ም በሀዋሳ ከተማ በተደረገው ሀገር አቀፍ ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር የፕሮጀክቱ ሴቶች ቡድን ዋንጫ ያነሳ ሲሆን የወንዶቹ ቡድንም የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡ በዚህም ከሁለቱም ቡድኖች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ክልሉን ወክለው የሚጫወቱ 16 ሴቶችንና 11 ወንዶችን አስመርጧል፡፡
አካዳሚው አገልግሎት መስጠት አቋርጦ የነበረውንና በቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ግቢ የሚገኘውን የመዋኛ ገንዳ አስፈላጊውን የዕድሳትና የማስዋብ ስራ በማጠናቀቅ ነሐሴ 5/2008 ዓ/ም ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል፡፡ የመዋኛ ገንዳው ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለስፖርታዊ ልምምድ፣ ለክልላዊና ሀገራዊ ውድድሮች፣ ለመዝናኛና ለተለያዩ ፕሮግራሞች ከማገልገሉ በተጨማሪ ለዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጭ እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራ ጎን ለጎን በስፖርቱ ዘርፍ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው፡፡ በስፖርት አካዳሚ በኩል እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች እንቅስቃሴዎች መንግስት በስፖርት የዳበረና ለተለያዩ ዓለም ዓቀፋዊ ውድድሮች ብቁ ወጣቶችን ለማፍራት ለጣለው ግብ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አላቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ስፖርት አፍቃሪዎች በማዕከላቱ ልምምዶችን በማድረግና አካዳሚው የሚሰጠውን ሌሎች የቁሳቁስ፣ የስልጠናና የማማከር አገልግሎት በመጠቀም ራሳቸውን ለሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ብቁ እንዲያደርጉ ፕሬዝደንቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡