የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹STEM›› ማስተባበሪያ ማዕከል ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ባስኬቶ፣ ጋርዱላ፣ አማሮ፣ አሌ እና ኮሬ ዞኖች ተወጣጥው  ከሐምሌ 13/2017 ዓ/ም ጀምሮ ለ45 ቀናት ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ 170 ተማሪዎች የሽኝት መርሐ ግብር ነሐሴ 30/2017 ዓ/ም አካሂዷል ፡፡ ሠልጣኝ ተማሪዎቹ ከ7ኛ- 11ኛ ክፍል የተወጣጡና በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት እንዲሁም የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የ‹‹STEM›› ሥልጠና መርሐ ግብር ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲን ሕይወት ቀድመው እንድያውቁ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎች ይህንን ዕድል ተጠቅመው ችሎታቸውን እንዲያወጡ እንዲሁም በትምህርት ቤቶቻቸው በግብአት እጥረት ምክንያት ያልተሸፈኑ የቤተ-ሙከራ የተግባር ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲው ያሉ ቤተ-ሙከራዎችን ተጠቅመው እንዲሸፍኑ ታልሞ የሚሰጥ ሥልጠና እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ በሠልጣኝ ተማሪዎች የቀረቡ የፈጠራ ሥራዎች ከመንግሥት አቅጣጫ ጋር ተመጋጋቢ እንዲሁም በአካባቢያችን የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚቻል አቅጣጫ የሚያሳዩ እንደሆኑም ዶ/ር ተክሉ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ ተማሪዎች መሰል የፈጠራ ሥራዎችን መስራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ም/ፕሬዝደንቱ አበረታተዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ‹‹STEM›› ማዕከል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ በቤተ-ሙከራ የተደገፉ ሥልጠናዎችን ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ የሚሰጠው ሥልጠና  ተማሪዎች ሳይንቲስት እና ኢንጂነር ብቻ እንዲሆኑ ማስቻል ሳይሆን ዕውቀትን ወደ ተግባር ቀይረው ችግር ፈች ዜጋ በመሆን የማኅበረሰቡን ችግር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚፈቱ እንዲሆኑ ማስቻል እንደሆነ ዶ/ር ቶሌራ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ‹‹STEM›› ሥልጠና ማዕከል አስተባባሪ ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም ባደረጉት ንግግር የሥልጠናው ዓላማ በሳይንስ ትምህርትና በፈጠራ ዘርፍ የተማሪዎችን ዕውቀትና ክሂሎት ማሳደግ ሲሆን ተማሪዎች በ45 ቀናት ቆይታቸው ሒሳብ፣ ፊዚክስ ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂን ጨምሮ ስድስት የሳይንስ ትምህርት ዓይነቶችን በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ከአይ ሲ ቲ እና ከሌሎች ዘርፎች ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በዋናው ግቢ በሚገኙ ቤተ-ሙከራዎች መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የላንቴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ በረከት ካሳሁን በሰጠው አስተያየት በማዕከሉ ስማርት የቆሻሻ ማጣሪያ የፈጠራ ሥራ መሥራቱን ተናግሮ በቆይታው የፕሮግራሚንግ ከሴንሰሮች ጋር የተገናኙ አሠራሮችን በተግባር ማየት እንደቻለ ተናግሯል፡፡ ይህም ቀጣይ ሊሰራ ላሳባቸው የፈጠራ ሥራዎች ይበልጥ ጠቃሚ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

በፕሮግራሙ መጨረሻ ለሠልጣኝ ተማሪዎች የምስክር-ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት