በሪፎርም አጀንዳዎች ዙሪያ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም የ2018 ዓ/ም መማር ማስተማር ሂደትን በተመለከተ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ከሳውላ ካምፓስ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ጥቅምት 12/2018 ዓ/ም ውይይት አካሂደዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው በለውጥ ጎዳና ላይ የሚገኝና ከምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ ለሀገር የሚጠቅሙ የምርምር ተግባራትን ለማከናወን ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሳውላ ካምፓስ ከአራት መቶ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የቤተ ሙከራ ግብአቶችን  ማሟላቱን የገለጹት ፕሬዝደንቱ መ/ራን በምርምር ሥራ ላይ በንቃት በመሳተፍ ከኅትመት ባሻገር መሬት ላይ ወርደው የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ራስ አገዝ መሆን አማራጭ የገቢ ምንጮችን በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ መምህራንና ሠራተኞችን መቅጠር  የሚያስችለው ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በርካታ ጠቀሜታዎችን ለተቋሙ እንደሚያስገኝ የገለጹት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ  በተቋሙ ተግባራዊ እየሆኑ  የሚገኙ ሁሉንም የሪፎርም አጀንዳዎችን የጋራ በማድረግ በትብብርና በትጋት ሰርቶ ተቋሙን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። 

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም አዋጅን መሠረት በማድርግ ከተቋማዊ ራስ ገዝነት፣ የመስክ ልይታ፣ የትምህርት ጥራት፣ የሥርዓተ-ትምህርትና አካዳሚክ መምሪያች ዝግጅትና ክለሳ ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ምርምር፣ አክሪዲቴሽን አንጻር እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል። ከላይ የተጠቀሱ የሪፎርም አጀንዳዎችን ለማሳካት ተነሣሽነት፣ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲሁም ከሀገርና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት ከተመራማሪዎች እንደሚጠበቅ ዶ/ር ተክሉ በገለጻቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማሪያም በበኩላቸው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በመጣበት በዚህ ዘመን የቴክኖሎጂ ዕውቀት አስፈላጊ መሆኑንና በዩኒቨርሲቲው የe-learning የማስተማር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸው  አዳዲስ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈት በሚቻልበት ሁናቴ በድኅረ ምረቃ ት/ቤት በኩል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የ2018 ዓ/ም መማር ማስተማር ሂደትን በተሻለ ማስኬድና ለሚሰጡ የምዘና ፈተናዎች በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጳውሎስ ታደሰ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው መልካም ሥነ ምግባር ያለው እና ውጤታማ ሠራተኛ መገንባት ከሪፎርም ሥራዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ጊዜው ለተቋሙ በእጅጉ ወሳኝ የሆኑ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች የሚሰሩበት ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ  በዚህ ረገድ የአስተዳዳር ዘርፉ ዕቅድን መሠረት ያደረገ ውጤት ተኮር ሥራ በመስራትና የአገልግሎት አሠጣጥን በማሻሻል  ለተቋሙ ራዕይ ስኬት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ በንግግራቸው አንስተዋል። ከሥራ ሰዓት አጠቃቀም ጋር እንደ ተቋም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ የሥራ ሰዓት አጠቃቀም የውስጥ መምሪያ ተዘጋጅቶ ከጥቅምት 1/2018 ዓ/ም ጀምሮ ሌሎች የሪፎርም ሥራዎችን በማካተት ተግባራዊ መሆን መጀመሩን በመድረኩ ያነሱት ፕ/ር ጳውሎስ መምሪያው በካምፓሱ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን አመራሩ በትኩረት እንዲሰራም አጽንዖት ሰጥተዋል።

በውይይቱ በሳምንቱ መጨረሻ የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞችን ተደራሸነት ማስፋፋት፣ የገቢ ምንጮችን ማሳደግ፣ ወቅታዊ የበጀት ድልድል ማድረግ፣ የስፖርትና መዝናኛ ሥፍራዎችን መፍጠር፣ በሠራተኞች የሥራ መደብ ድልደላና ቅሬታ አፈታት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄዎች ተነሥተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ 

 

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት