1ኛው አገር አቀፍ የህግ ማስከበር እና 2ኛው የወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ሳይንስ ዓውደ ጥናት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዘጋጅነት ከታኅሣሥ 25-26/2011 ዓ/ም በኮሌጁ ተካሂዷል፡፡ የከፍተኛ ትምህርትና ሌሎች የተለያዩ ተቋማት ከሚያካሂዱት የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ምርመራ ጥናት ልምድ ለመቅሰምና ለሌሎች ለማካፈል፣ የአገራችንን የፎረንሲክ ምርመራ እድገት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ የማኅበረሰብ ፖሊስ ቁጥጥር ሥራዎችና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም አገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን ዓይነትና መንስኤዎች በመለየት የአገሪቱ የህግ አከባበር ሥርዓት በተገቢው መንገድ እንዲመራ ለማድረግ ዓውደ ጥናቱ ተዘጋጅቷል፡፡ በዓውደ ጥናቱ የሁለት ቀናት ቆይታ በፎረንሲክ ሣይንስ 3 እና በህግ ማስከበር 7 በድምሩ 10 ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ከ360 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት አቶ አየለ ሙሉጌታ በዓውደ ጥናቱ የተለያዩ ምርምሮች መቅረባቸው በተለይ በፎረንሲክ ሳይንስ የሚደረገውን ምርምር ከማጠናከር ባሻገር ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የአገሪቱን የፍትህ አሠራር ለማዘመን የሚያስችልና የተመራማሪዎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር እውቀትና ተሞክሯቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ፎረንሲክ ሳይንስ የወንጀል ምርመራ ሳይንስ ነው ያሉት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ ዘርፉን በአገራችን ለማስፋፋትና ለማዘመን ምርምሮችና ተያያዥ ሥራዎች በስፋት ቢካሄዱ በወንጀል ምርመራና በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዶ/ር ፈቃዱ አብራርተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘርፉን ለማጠናከር የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በመክፈት ለተማሪዎች በቤተ-ሙከራ የታገዘ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን የዚህ አውደ-ጥናት መካሄድም ከምሁራን የተሻለ ልምድ በመቅሰም ለአገሪቱ ብቁ ዜጎችን ለማበርከት እንደሚያስችለው ዶ/ር ፈቃዱ ጠቁመዋል፡፡
የፎረንሲክ ሳይንስ በተለይ በፖሊስ ተቋማት ተዓማኒና ቀልጣፋ ፍትህ እንዲኖር ትልቅ ፋይዳ ቢኖረውም በአገራችን የፖሊስ ተቋማት ተስፋፍቶ እየተሠራበት እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም በዘርፉ በበቂ ሁኔታ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የማሽኖች አለመሟላት፣ የቤተ-ሙከራ እጥረት፣ የመንግሥት ትኩረት ማነስ እና የሰዎች የግንዛቤ ክፍተት ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ሳይንስ ዳይሬክተር ተወካይ ኮማንደር አሰፋ ተገኑ የፎረንሲክ ሳይንስ ማስረጃዎች እውነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችን የሚሰጡ ሲሆን የፍትህ ሥርዓቱን ለማሳለጥና ትክክለኛ ፍትህ ለማስገኘት ጠቃሚ መሆናቸውን በተለይም ወንጀል ያልፈጸመ ሰው ያለ ወንጀሉ እንዳይሰቃይና እንግልት እንዳይደርስበት የተሻለ መፍትሄ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ የDNA፣ የአሻራ፣ የሰነድ፣ የባዮኬሚካልና የደም ዓይነት ትክክለኛ የምርመራ ውጤት ለማስገኘት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ኮማንደር አሰፋ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኮማንደሩ ገለፃ ኮሌጁ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ያጠናቀቁ 5 ተማሪዎችን በመቀበል ፖሊሳዊ ስልጠና ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡ በኮሌጁ ትምህርታቸውን ተከታትለው ካጠናቀቁ ሰልጣኞች 5ቱን ለአጫጭር ስልጠና ወደ ህንድ ልኮ ልምድ እንዲቀስሙም አድርጓል፡፡
ኮሌጁ ታኅሣሥ 27/2011 ዓ.ም በ2ኛ ዙር 50 የወንጀል መርማሪዎችን በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ዙር 33 የወንጀል መርማሪዎችን በጀኔሪክ ዲግሪ እንዲሁም በተለያዩ ፖሊሳዊ ስልጠናዎች 206 የፖሊስ ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡ ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በ4 ትምህርት ክፍሎች በዲፕሎማና በዲግሪ 250 ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
በዓውደ ጥናቱ ከአርባ ምንጭና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሰንዳፋ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ዳይሬክቶሬት፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ከኢትዮጵያ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተወጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡