በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ በሀገራችን ለ18ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም ዓቀፍ የፀረ-ሙስና  ቀን  በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ9ኛ ጊዜ ‹‹ሙስናን መታገል በተግባር!››  በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 26-27/2015 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በፕሮግራሙም የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር ግቢ ከማጽዳት ጀምሮ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር፣ ዕለቱን አስመልክቶ የተለያዩ ሰነዶች፣ ግጥሞችና መነባንቦች ቀርበዋል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የሥነ ምግባር መርሆዎችን በአግባቡ በመተግበር ለሙስና ስጋት የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ መንስዔዎችን ከምንጫቸው በመንቀል በአገልጋይነት መንፈስ ተቋማዊ ሚናችንን በመወጣት አርዓያ ልንሆን ይገባል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምነቱ የፀረ-ሙስና ትግሉን በመደገፍና በጋራ በመታገል ምቹ የትምህርት አካባቢን ለመፍጠር በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን እንደተናገሩት የሙስናን ምንነትና የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ከማወቅና ከመረዳት ባሻገር ድርጊቶቹን ባለመፈፀም፣ ሲፈፀም አምርሮ በመታገልና በማጋለጥ እንዲሁም ከንግግር ባለፈ የተግባር ሰው በመሆን ሙስናን በጋራ ልንታገል ይገባል፡፡

እንደ ወ/ሮ እታፈራሁ ገለጻ የፀረ-ሙስና ቀን መከበሩ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ሠራተኛ ሙስና እያስከተለ ያለውን ዓለም አቀፋዊ  አስከፊ ገፅታ ተረድቶ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ጥረት እንዲረዳ እና የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን ላይ የተደነገጉ የሥነ ምግባር ግንባታና ሙስናን የመከላከል ድንጋጌዎችን ተግባራዊ በማድረግ ትግሉን ለለውጥ ለማጠናከር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሯ አክለውም በመልካም ስብዕና የታነጸ እና በዕውቀት የተገነባ አምራች ዜጋን ማፍራት፣ የተቋሙን ማኅበራዊ ደኅንነትና ሕልውና ሠላማዊ እና የተረጋጋ እንዲሁም በሕግና ሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ማድረግ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ሥነ-ምግባርንና ፀረ-ሙስናን አስመልክቶ ለፓናል ውይይት መነሻ የሚሆኑ በሀገራችን የተጠኑ ጥናቶች በሕግ ት/ቤት መምህራን የቀረቡ ሲሆን በጥያቄና መልስ ውድድሩ ተሳትፈው ከ1ኛ- 4ኛ ለወጡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡
በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት