በኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አማካኝነት የስፓኒሽ ኤጀንሲ “Agency for International Development Cooperation/AECID” ለዩኒቨርሲቲው አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች አገልግሎት የሚውሉ 16 ኮምፒውተሮች ከነወንበርና ጠረጴዛቸው፣ አንድ የቀለም ፕሪንተር፣ አንድ የፎቶኮፒ ማሽን፣ አንድ ፕሮጀክተር፣ ሦስት የዋይፋይ ራውተርና ሌሎች አጋዥ ግብዓቶችን ኅዳር 28/2016 ዓ/ም አበርክቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደ ተቋም ሴት ተማሪዎች ላይ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉ ጠቁመው በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ተግባራት የሚከወኑት በቴክኖለጂ ተደግፈው በመሆኑ ድጋፉ ውጤታማ ለመሆን ያግዛል ብለዋል፡፡ የተማሪዎች የቴክኖሎጂ ዕውቀት የተለያየ እንደመሆኑ መጠን በተለይም ከገጠርና ከሩቅ  አካባቢ የሚመጡ ሴት ተማሪዎች የኮምፒውተር የተግባር ልምድ የሌላቸው ሊኖሩ ስለሚችሉ ልየታ በማድረግና ብዙ ድጋፍ ለሚሹ ቅድሚያ በመስጠት እንዲገለገሉ ማድረግ እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡  በቀጣይም ተማሪዎቹን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቱ አክለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ያደጉ ሀገራት ያላቸውን የትምህርት ተሞክሮ ማየቱ ጠቃሚ እንደሆነና የተደረገው ድጋፍም ወደ እዚያው ለመቅረብ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረው ግብዓቱ በቤተ-መጽሐፍት መቀመጡና ሰፊ የኢንተርኔት ስርጭት መኖሩ ለማንበብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዓለማየሁ አክለውም የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎች የንብረቱን ደኅንነት የማስጠበቅና ተማሪዎቹ በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ድጋፉ በኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኩል ከስፓኒሽ ኤጀንሲ የተገኘ ሲሆን በዚህም አርባ ምንጭ፣ ደብረ ታቦርና መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች ተለይተው የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች በአብዛኛው በመጀመሪያ ዓመት ላይ የሚያጋጥሟቸውን የኮምፒውተርና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎት ችግር ለመቅረፍም የተለያዩ ሥልጠናዎችና ድጋፎች እንዲያገኙ በኢፌዲሪ ፕሬዝደንት በኩል መደረጉን ዳይሬክተሯ አመላክተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው በኩል ሴት ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት