አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹USAID-Feed the Future Ethiopia Transforming Agriculture›› ጋር በመተባበር በኦሮሚያ፣ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከሚገኙ ማኅበራት ለተወጣጡ ተወካዮች የእንሰት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከግንቦት 21-25/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በ‹‹Feed the Future Ethiopia Transforming Agriculture›› የሥነ ምግብ ማኔጀር አብነት ሽፈራው ከእንሰት ተክል የሚገኙትን ቡላ እና ቆጮ በመጠቀም ኬክ፣ ኩኪስ፣ ዳቦና ሌሎችም ምግቦችን ብሎም ሞሪንጋ፣ አኩሪ አተርና ማሽላ በማቀላቀል ለሕፃናትና ለወላድ እናቶች ተስማሚ፣ የምግብ ይዘቱ ከፍ ያለና ጣዕሙ ጥሩ የሆነ ምግብ ማዘጋጀት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የባዮቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንደገለጹት ሥልጠናው የእንሰት ማቀነባበሪያ ማሽን አጠቃቀም እና ከእንሰት የሚገኘው ቡላ፣ ቆጮና የእንሰት እርሾ አመራረትን ከምግብ ደኅንነት አንጻር ጭምር ያካተተ የተግባርና የልምድ ልውውጥ መድረክ ነው፡፡ ሥልጠናው ቴክኖሎጂውን በመላው ኢትዮጵያ ለማዳረስ ያለመ መሆኑን ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡ከ‹‹USAID-Feed the Future Ethiopia Transforming Agriculture›› በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ማሽኑን አግኝተው ምርቱን ወደ ገበያ ይዘው እንደሚወጡ የጠቆሙት ተመራማሪው ይህም ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥርና ለረዥም ዓመታት በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋለውን የእንሰት ተክል በሰፊው አምርቶ ወደ ምግብ ሥርዓት እንዲገባ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የባዮሎጂ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አሠልጣኝ አወቀ ማሞ እና በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶራ ወረዳ ‹‹አንድነት የእንሰት መፋቂያ ማኅበር›› አባል አሠልጣኝ ወንድሙ ኮልባይ ዘመናዊ የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የእንሰት ግንድ አፋፋቅ፣ የቃጫ አወጣጥ፣ የአምቾ አፈጫጭና አጨማመቅ ሂደት እንዲሁም ቆጮን በማብላያ ውስጥ የማብላላትና የቡላ አመራረት ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡
ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው የዘመናዊ እንሰት ማቀነባበሪያ ማሽን አጠቃቀም፣ የቆጮ እርሾ አሠራር፣ ከቃጫ የሚሠሩ የእጅ ሥራዎች እንዲሁም ከቆጮና ከቡላ የሚሠሩ የምግብ ዓይነቶችን በሚገባ ማየታቸውንና እንሰትን በዘመናዊ መንገድ አቀናብሮ ለተጠቃሚው ለማድረስ የሚያስችል ዕውቀት መገብየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት