አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ‹‹Public Entrepreneurship and Innovation Ecosystem Building›› በሚል ርዕስ በዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቪ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሚሠሩ የአስተዳደርና ክሊኒካል የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከሐምሌ 11-13/2016 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ሆስፒታሉ አዲስ እንደመሆኑ ከዚህ ቀደምም በተቋሙ ለመሥራት ለተዘጋጁ የጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ መሰል ሥልጠናዎች በሆስፒታሉ የሚሠሩ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ዘመኑን በዋጁ አስተሳሰቦችና ዕውቀቶች የተቃኙ እንዲሆኑ በማድረግ ሆስፒታሉ በስሙ ልክ ጥራት ያለውና የደንበኞችን ፍላጎት የሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡ መሰል ሥልጠናዎች በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ዶ/ር ደስታ ጠቁመዋል፡፡

በሆስፒታሉ የሕክምና ትምህርትና አገልግሎት ጥራት ኮርፖሬት ዳይሬክተርና የሥልጠናው አስተባባሪ ወ/ሮ ስንታየሁ አበበ በበኩላቸው ሥልጠናው በዋናነት በሁሉም ደረጃ በሆስፒታሉ የሚሠሩ ሠራተኞችና  ባለሙያዎች ደንበኛን ከመቀበል አንስቶ ለታካሚዎች ተገቢውን አክብሮት፣ እንክብካቤና አገልግሎት የመስጠት ወጥ እሳቤ እንዲያጎለብቱ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ በሥልጠናው በሆስፒታሉ የሚሰሩ የጥበቃ፣ የጽዳትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ጨምሮ በተለያዩ የሕክምና ክፍሎች የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች፣ ሐኪሞች እንዲሁም የየዘርፉ ኃላፊዎች የተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ እንደገለጹት ብዙን ጊዜ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከአገልግሎት ጥራት፣ ከደምበኞች እርካታ፣ ከሀብት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች በስፋት ይነሳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ሥልጠናው በዋናነት ወጥ በሆነ አስተሳሰብ በጋራ የመሥራት፣ ደንበኞችን ታሳቢ ያደረገ ጥራት ያለው አገልግሎት የመዘርጋት እንዲሁም ከተለመደው አካሄድ የተለየና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት በተቋሙ እንዲኖር የሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች የተዳሰሱበት መሆኑንና በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚቀርፉ መሆናቸውን ዶ/ር ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው ጥሩ ግንዛቤ ያገኙበትና ለቀጣይ ሥራቸው አጋዥ የሆኑ አዳዲስ አስተሳሰቦችን የተገነዘቡበበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት