የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ የተደገፈ የፍትሕ ሥርዓት ለማስፈን የሚረዳ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከልን የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር መስከረም 13/2017 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ዩኒቨርሲቲው በፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ የትምህርት ዘርፎች በቅድመና ድኅረ ምረቃ የትምህርት ደረጃዎች በርካታ ምሁራንን እያፈራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ወንጀል በረቀቀበት በዚህ ዘመን ኢ-ፍትሐዊነት እንዳይፈጠር፣ ዘመን የሚዋጁ መሳሪያዎችን በመጠቀም መረጃን በማግኘት ፍትሕና እውነት እንዳይደበቁ ከማድረግ አንፃር በዩኒቨርሲቲው የተከፈተው ማዕከል ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረክታል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ በበኩላቸው የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከሉ መከፈት እና ሥራ መጀመር አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ የሚባክነውን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ሥራ እንዲቀላጠፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የፍትሕ ሥርዓት መዘርጋትና ማስፈን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  የፍትሕ ሥርዓቱን አፈፃፀም ይበልጥ ለማሻሻልና ውጤታማ ለማድረግ የአሠራር ሥርዓቶችን ማዘመንና በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ ይገባል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ከዚህ አንፃር  በዩኒቨርሲቲያችን ሥራ የጀመረው የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል የጎላ ሚና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ የሐሰተኛ ሰነዶች፣ የባዮ-ኬሚካል፣ ቶክሲኮሎጂ፣ የእጅ ጽሑፍ፣ ፊርማ፣ ድልዝ፣ የተጨመሩ፣ የተቀነሱ፣ የማህተምና የቲተር፣ የባንክ ኖቶች፣ ፓስፖርቶች ቼኮችና የትምህርት ማስረጃዎች  ላይ የሰነድ ምርመራዎች እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት