የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ የካውንስል አባላት በተገኙበት ነሐሴ 29/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ግምገማው ዓመታዊ ዕቅዱን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት አድርጎ በማቀድ በተገቢው መንገድ ለመሥራትና ለመመራት እንዲሁም በወቅቱ የጠራ ሪፖርት ለማቅረብ እንደሚረዳ ገልጸው ዕቅዱ ከመድረኩ የተገኙ አስተያየቶች ተካተው የሚዳብር መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ክንውንና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ በ8 ዋና ዋና ግቦች የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀትን ማጣጣምና ማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የሳይንስ ባህል ግንባታ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማሳደግ፣ የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግ፣ ተቋማዊ የማስፈፀም አቅም፣ የሀብት አጠቃቀምና የአገልግሎት አሰጣጥ አሠራርን ማጎልበት፣ የትምህርት ተቋማዊ አቅምና ብቃት ማጎልበት፣ ተቋማዊ መሠረተ ልማት፣ ፋሲሊቲና እና ግብአትን ማሳደግ እንዲሁም የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ውጤታማነትን ማሳደግ ላይ ስትራቴጂክ ዕቅዶችን አቅርበዋል፡፡

ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ መደበኛ በጀት 1,531,477,648 እና ካፒታል በጀት 600,000,600 በድምሩ 2,131,478,248 ብር ተፈቅዶ የተመደበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወልደመድኅን የተጀመሩ ግንባታዎችን በአፋጣኝ ለማስጨረስ የሚመደበው በጀት በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው እንደ ሀገር ያለውን የበጀት እጥረት በማቻቻል በሚመደበው በጀት ሥራው እንዳይቆም በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የኃላፊነት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት የማኅረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በድኅረ ምረቃ ት/ቤት አስተባባሪነት እንዲሁም የድኅረ ምረቃ ት/ቤት አስተባባሪ የነበሩት ዶ/ር አበራ ኡንቻ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን በመሆን ቀጣይ የሥራ ኃላፊነት መቀበላቸው ተገልጿል፡፡ ኃላፊዎቹ በቀድሞ የሥራ ዘመናት ለተቋሙ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ የተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም ክትትልና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችን ለካውንስል አባላት አቅርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት