የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አይዪሲ ፕሮጀክት (AMU-IUC) በሁለተኛ ምዕራፍ የምርምር ውጤቶችን ወደ ማኅበረሰብ የማውረድ ፕሮግራም (Research Outreach) ከቦረዳ፣ ጨንቻ ዙሪያ፣ ጋጮ ባባ፣ ገረሴ፣ ካምባ፣ ቦንኬ እና ቆጎታ ወረዳዎች ለተወጣጡ እንሰት አብቃይ ሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ከታኅሣሥ 23-24/2017 ዓ/ም የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የAMU-IUC ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከአምስት የቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የሚሠራ ሲሆን በፕሮጀክቱ አማካኝነት የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው የጨረሱ ተመራማሪዎች ሳይንሳዊ የምርምር ግኝቶቻቸውን ወደ ማኅበረሰቡ ያወርዳሉ፡፡ የጥናት ውጤቶች ተግባራዊ ሆነው ነባራዊውን ችግር መቅረፍና የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር አለባቸው ያሉት ማኔጀሩ ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሩን ሀገር በቀል ዕውቀት ለረዥም ዓመት ተለፍቶባቸው በምርምር ከተገኙ ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር በማጣመር ለውጥ ለማምጣት ይሠራል ብለዋል፡፡

ከAMU-IUC ፕሮጀክቶች መካከል የግብርና ምርታማነት ላይ የሚሠራው ንዑስ ፕሮጀክት V መሪ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ በፕሮጀክቱ ሦስት መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውንና ሁለቱ በትምህርት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው መምህራኑ በእንሰት ተክልና በእንስሳት ሥነ ምግብ ላይ በማተኮር የሠሯቸውን ምርምሮች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

እንደ ፕ/ር ይስሃቅ 20 ሚሊየን ያህል እንሰት አምራች አርሶ አደር በሀገራችን ቢኖርም በበሽታ፣ በምርታማነት ማነስ እንዲሁም ዘርፉ በምርምርና ግብርና ኤክስቴንሽን ያልተደገፈ በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ምርት እያስገኘ አይደለም፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ውጤታማ ምርምሮችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች መሥራቱን የጠቀሱት ፕ/ር ይስሃቅ በሥልጠና፣ በአርሶ አደር ማሳ ሙከራ በማካሄድና ችግኞችን አባዝቶ በመስጠት በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ወደ መሬት ለማውረድ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ 

የወተት ሀብት ልማት ሌላው ትኩረታቸው መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው ተመጣጣኝ ያልሆነውን የወተት ፍላጎትና አቅርቦት ለማሻሻል በሙከራ የተረጋገጡ የሳይንስ ውጤቶችን ለግብርና ባለሙያዎችና ለሞዴል አርሶ አደሮች በማጋራት የማነቃቃትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በሥልጠናው ከንድፈ ሃሳብ በተጨማሪ በኮሌጁ እና በተለያዩ ቀበሌያት ባሉ የሙከራ ጣቢያዎች የሚሠራውን ድርቆሽ፣ ገፈራና የተመጣጠነ መኖ ከተለያዩ ዕፅዋት መጥኖ የማዘጋጀት ሒደት እንዲሁም የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን፣ ከእንሰት ምርት የተዘጋጁ ኬክ፣ ኩኪስና ሌሎችም ምግቦችን ሠልጣኞች በተግባር መመልከት መቻላቸውን ፕ/ር ይስሃቅ ተናግረዋል፡፡

የእንስሳት ሥነ ምግብ ተመራማሪ የሆኑት አሠልጣኝ ዶ/ር አሸናፊ አዛገ በሀገር አቀፍ ደረጃ የእንስሳት መኖ እጥረት መኖሩን ጠቅሰው እጥረቱ በሚከሰት ጊዜ ከምርት መቀነስ ባሻገር እንስሳቱን እስከማጣት እንደሚያደርስ ገልጸዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው በአካባቢው አርሶ አደሩ በልምድ የሚሠራበት የመኖ ማቆያ ዘዴ የሰብል ተረፈ ምርቶችን በማድረቅ ሲሆን ይህም ለጥራት ጉድለት የተጋለጠ፣ እስከ ሦስት በመቶ ብቻ ፕሮቲን የያዘና የምግብ ይዘቱ የቀነሰ ነው፡፡ አንድ እንስሳ  ምግቡን አስተካክሎ ለመፍጨት ሰባት በመቶና ከዚያ በላይ ፕሮቲን ይፈልጋል ያሉት ተመራማሪው አርሶ አደሩ ብዙ መኖ  በሚኖርበት ጊዜ ሰብስቦ ጥራቱን ጠብቆ አስፈላጊውን ፕሮቲን እንደያዘ ማቆየት በሚችልበት ዘዴ ላይ ሥልጠና መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞቹ የበቆሎ አገዳና ሌሎች ዕፅዋት በአረንጓዴነታቸው ሳሉ ቀረጣጥፎ አየር በማያስገባ መንገድ በማብላላት የሚገኘው ገፈራ/Silage/ አዘገጃጀት ላይ ተግባራዊ ሥልጠና ያገኙ ሲሆን ይህም በእንስሳቱ ጤንነት፣ በወተትና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦ ጥራት፣ በሕፃናት ጤንነትና እድገት እንዲሁም በሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ረገድ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራተዋል፡፡

ሌላኛው አሠልጣኝ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ የምርምራቸው ትኩረት በሆነው የእንሰት አጠውልግ በሽታ/Bacterial Wilt/ ምልክቶች፣ መተላለፊያ መንገዶች እና የመከላከያና የመቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን አርሶ አደሩ እንሰትን በቤት ውስጥ ከመጠቀም ባሻገር በሰፊው አምርቶ ለገበያ ማቅረብ የሚችልበትን መንገድም ዳስሰዋል፡፡ ተመራማሪው እንዳብራሩት በእንሰት ምርት አመራረት ላይ ከሚገጥሙ ችግሮች አንዱና ዋነኛው የሆነው የእንሰት አጠውልግ በሽታ ለረዥም ጊዜ መፍትሔ ያልተገኘለት ቢሆንም መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል፡፡ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ምልክቶችን በቀላሉ መለየት፣ የበሽታውን ባሕርይ፣ የመተላለፊያ መንገዶችና የሚያባብሱ ነገሮች፣ በተለይም ከሥነ ምኅዳር ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች የበሽታው ስፋትና አደገኛነት እንዲሁም የመከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ የአርሶ አደሩን ልምድና ሳይንሳዊ ግኝቶችን በማጣመር በሥልጠናው ሰፊ ውይይት መደረጉን ዶ/ር ሳቡራ ገልጸዋል፡፡

የሆርቲካልቸር ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ሌላኛው አሠልጣኝ ዶ/ር ገዛኸኝ ጋሮ የእንሰት በሽታ ከሚተላለፍበት መንገድ አንዱ ችግኞችን በሽታው ካለበት እርሻ ወስዶ መጠቀም መሆኑን ተናግረው ሥልጠናው ያለንክኪ ከበሽታ የጸዳ ችግኝ አባዝቶ ለመጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ ግንዛቤ ያስጨበጠ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል አርሶ አደሩ እንሰትን ለማሳደግ የእንስሳት ፍግ እንደሚጠቀም ያወሱት ተመራማሪው ፍጉን በተክሉ ላይ  ከመጨመራቸው በፊት ውጪ ላይ ከምረው ሲያቆዩ ንጥረ ነገሮች በትነትና በስርገት የሚጠፉ በመሆኑ ተክሉ የሚያገኘው ንጥረ ነገር የተዳከመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 
ዶ/ር ገዛኸኝ ፍጉን ጉድጓድ አዘጋጅቶና በላስቲክ ሸፍኖ ማስቀመጥ ንጥረ ነገሩ እንደተጠበቀ ለማቆየት የሚረዳ መሆኑን በምርምራቸው የጠቆሙ ሲሆን ይህንን ዘዴ ለአርሶ አደሩ በማጋራት የእንሰት ምርታማነትን ለማሳገድ ከሥልጠና ባሻገር በተመረጡ ቦታዎች አርሶ አደሩጋ ወርደው እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሥልጠናው የተሳተፉ አርሶ አደሮች ለረዥም ጊዜ ከእንሰት ጋር ባላቸውን ቁርኝት ያገኙትን ልምድ በመድረኩ ያጋሩ ሲሆን በተለይም የእንሰት በሽታ መነሻ፣ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ላይ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመቅረፍ የሚረዳ ዕውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተግባር ባዩት የእንሰት ቴክኖሎጂዎች፣ የእንሰት ምግቦች እና የመኖ አዘገጃጀት ሒደት መደሰታቸውንም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት