በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የምርምርና ድኅረ ምረቃ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ቋንቋዎች በማዳን ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ እንዲችሉ ውጤታማ ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በቋንቋ ላይ የሚያካሂዳቸው ምርምሮች ቋንቋውን ከመጠበቅ የመድኃኒትና መሰል ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመሰነድ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ እንዲቻል ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ በቋንቋና ባህል በቂ ምርምር የማካሄድና የመሰነድ ሥራ ካልተሠራ ቋንቋውና ባህሉ ተያይዘው እንደሚጠፉ ‹‹የጋፋት›› ቋንቋን ምሳሌ በመጥቀስ አስገንዝበዋል፡፡ ሀገር በቀል ዕውቀቶች የሀገር ሀብት በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚያካሂደውን ምርምር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የምርምርና ድኅረ ምረቃ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተቀመጠለትን ሀገራዊ ተልእኮ ለማሳካት የማኅበረሰቡን መልካም እሴት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚካሄደው ጥናት የተሻለ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡
እንደ ዶ/ር እንዳልካቸው በደቡብ ኦሞ ዞን በና ጸማይ ወረዳ እጨንቴ ቀበሌ ከሚኖሩት 427 ተወላጆች መካከል 6ቱ ብቻ የኦንጎታ ቋንቋ የሚጠቀሙበት በመሆኑ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በምርምር በመታገዝ መዝገበ ቃላት የማዘጋጀት፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና ሥነ ቃሎችን የመሰነድ እና የመገምገም እንዲሁም ቋንቋውን በጎልማሶች ትምህርት እና በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ሥርዓት በማካተት የአካባቢው ተወላጆች እንዲማሩት በማድረግ የማዳን ሥራ እየሠራ የሚገኝ መሆኑን ዶ/ር እንዳልካቻው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ከብሔረሰቡ የእለት ተእለት አኗኗር ጋር በተያያዘ በቂ ምርምር ለማከናወን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሥነ ልሣን መ/ር እና የኦንጎታ ቋንቋ ተመራማሪ ዶ/ር ስንታየሁ ሰሙ በቋንቋ ላይ የሚካሄዱ ምርምሮች ማኅበረሰቡን ከመጥፋት መታደግ የሚያስችሉ በመሆናቸው በቋንቋ ጥናት ላይ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶች ሊስተካከሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ቋንቋ ከመታደግ ጋር በተያያዘ መዝገበ ቃላትን የማዘጋጀትና መማሪያ መጻሕፍትን የማሳተም ሥራ እንዲሁም በቀጣይ ለሚከናወኑ ምርምሮች ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
የኮይጉ ቋንቋ ተመራማሪ ዶ/ር ዳኘው ማቸ በበኩላቸው በቋንቋና ባህል ጥበቃ ላይ የሚከናወኑ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ባህልና እሴት አስጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ኮይጉኛ በኛንጋቶም ወረዳ ኩችሩ ቀበሌ 1500 ያህል ተናጋሪ ያሉት ሲሆን በአካባቢው በስፋት በሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎች የመዋጥና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን ተመራማሪው አብራርተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቋንቋው መዝገበ ቃላትን፣ ሰዋስው፣ ቃላዊ ትውፊቶችን፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን የመሰነድ እንዲሁም የመማሪያና ማስተማሪያ መጻሕፍት የማዘጋጀት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ዳኘው ጠቁመዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት