አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ጋር በመተባበር የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት መንስዔዎች፣ የሚያስከትለው ጉዳትና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የሠራውን የጥናት ሰነድ ጥር 29/2017 ዓ/ም ርክክብ አካሂዷል፡፡ በዕለቱ ከምርምሩ በተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዋኖ ዋሎሌ የወጣቶች ለአደገኛ ሱስ ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱ ጥናቱን ለማካሄድ አነሳሽ ምክንያት መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥልቅ መረጃን በማመላከት ውጤት ማምጣት የሚያስችል ጥናት ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ እንደ ቢሮ ኃላፊው በቀጣይም በቀረበው መረጃ መነሻት ግልጽና አጭር የፖሊሲ አቅጣጫ፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አዋጆች እንደ አስፈላጊነቱ የሚወጡ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የማኅበረሰቡን የተቀናጀ ሥራ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎምባ ደምሴ እንደገለጹት የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ቢኖረውም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የጠለቀ ይዘት ያለው በመሆኑ አፋጣኝና የተቀናጀ መፍትሔ ካልተበጀለት ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነት በከተሞች ላይ በስፋት የሚታይ ቢሆንም እስከ ታዳጊ ከተሞች ዘልቆ የመስፋፋት ዕድሉ እየጎላ መምጣቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የጥናት ውጤቱን በመጠቀም ለችግሩ ተጋላጭ ዜጎችን የመታደግና አምራችና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራ በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጸው ለዩኒቨርሲቲው፣ ለጥናት ቡድኑና ለጥናቱ ስኬት በጎ አስተዋጾ ላበረከቱ ሁሉ ልባዊ ምስጋናቸውን ኃላፊው አቅርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም የተሠራውን የጥናት ውጤት ርክክብ ለማድረግ እንዲሁም ከጥናቱ በተገኘው ውጤት ላይ ተመሥርቶ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ከጥናቱ የተገኘው የመፍትሔ ሃሳብ ወሳኝ በመሆኑ ከመረካከቡ ባሻገር ለትግበራው በሚረዱ ሃሳቦች ላይ አቀጣጫ መቀመጣቸውን ተናግረው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከምርምር የሚገኙ ውጤቶች ላይ ተቀራርበው መሥራታቸው ሀገርን ለመለወጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡ ለጥናቱ አንድ ሚሊየን አምስት መቶ ሺህ ብር በጀት መመደቡንና ከዚህም ውስጥ አንድ ሚሊየኑ በዩኒቨርሲቲው እና ቀሪው ብር በሁለቱ የክልል መሥሪያ ቤቶች መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር የቀድሞ ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የቀድሞው የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ባወጣው ውድድር ጥናቱን ለማካሄድ ዩኒቨርሲቲው አሸንፎ ሥራውን መጀመሩን አስታውሰው የጥናት ውጤቱ በአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነት ላይ አስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ መጠቆሙን ተናግረዋል፡፡ተ/ፕ በኃይሉ በዩኒቨርሲቲው በአዕምሮ ውቅርና በሥነ ልቦና ላይ ሥልጠናዎችን የመስጠት ጅምር ሥራ መኖሩን ጠቅሰው በርካታ ያልተዳሰሱና ያልተነኩ የማኅበራዊ ጉዳይ ችግሮችን ለመፍታት ተቀራርቦና ተባባሮ በመሥራት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የጥናት ቡድኑ መሪ ፍርዳወቅ ጌታሁን ጥናቱ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ሥርጭት፣ ወደ ሱስ እንዲገቡ የሚገፋፉ ምክንያቶች እና እያስከተለ ያለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት ላይ ትኩረት አድርጎ ከ10-29 ዓመት ያሉ አፍላ ወጣቶች ላይ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ የአቻ ግፊቶች፣ አደንዛዥ ዕፅ በቅርበትና በአካባቢ መኖር፣ የሥራ ዕድል ያለመኖር፣ የሕግ ክፍተትና የቁጥጥር መላላት ወደ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም ከሚገፉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ተመራማሪው ችግሩ ከግለሰብ እስከ ሀገር የሚዘልቅ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዳለው በጥናቱ ማየት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ የችግሩ መፍትሔ ያሏቸውን ሃሳቦች በጥናቱ መጠቆሙንና ችግሩን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት አቅዶ መሥራት እንደሚገባ ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጥናቱ ሀገር ለማዳንና ትውልድን ለመታደግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረው አምራች ዜጋ የሆነውን ወጣት ለመታደግ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መሥራት የሁሉም ማኅበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዕለቱ የስርጸት እና የፕሮጀክት ትግበራ ቡድን የተመሠረተ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሪነት የጥናት ቡድኑ አባላት እና ከሁለቱም የክልል መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ አካላት አዲስ ቡድን ተዋቅሮ ሥራውን ለማስቀጠል ስምምነት አድርገዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት