የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከየ "United Nations Office of High Commission for Refugees/UNHCR" ጋር በመተባበር ከኮንሶ፣ አሌ፣ ጋርዱላ እና ጋሞ ዞኖች ከተወጣጡ የፍርድ ቤት ዳኞች ጋር የካቲት 1/2017 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክክር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተወካይና የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተደገፉ በርካታ ማኀበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሕግ ትምህርት ቤት በኩል በተለያዩ ቦታዎች የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም በፍትሕ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመንና ፍትሐዊ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ሦስቱ ተልእኮዎችን ባማከለ መንገድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የውይይት መድረኩ በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ከሚሠሩ ተግባራት መካከል መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ በቀጣይም የኅብረተሰቡን ችግር መነሻ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም አብራርተዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት አቶ አንዷለም አምባዬ በበኩላቸው ክልሉ በአዲስ መንገድ ሲደራጅ ከተሻሻሉ አዋጆች አንዱ የገጠር መሬት አዋጅ መሆኑን ገልጸው የተሻሻለው አዋጅ የቀድሞው አዋጅ የነበሩበትን ክፍተቶች የሚሞላ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በአዋጁ ዙሪያ ያዘጋጃው የውይይት መድረክ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የሕግ ት/ቤት ዲን ተወካይና የሕግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አብርሃም ክንፈ መሬት ትልቅ ሀብት እንደመሆኑ በርካታ ክርክሮች የሚነሱበት ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲስ በወጣው አዋጅ ላይ የፍትሕ አካላትን ግንዛቤ ለማዳበርና ዳኞች በሚገጥሟቸው ክርክሮች ላይ የተስተካከለ ፍትሕ አንዲሰጡ ለማስቻል እንዲሁም ብዥታ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ለማጥራትና ዳኞች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ ታልሞ መድረኩ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
በዕለቱ በክልሉ የገጠር መሬት አዋጅ ላይ የተሠራ ጥናታዊ ጽሑፍ በመ/ር ባላቴ ብሳሬ ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎችም አዋጆች የሚለዋወጡና የሚሻሻሉ በመሆኑ ከመሬት አዋጁ ጋር በተያያዘና ከክልል አልፎ ሀገራዊ በሆኑ ሕጎች ላይ ወቅታዊ የሆኑ አዳዲስ መረጃዎችን እንድናገኝ መድረኩ ዕድል ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡ መሰል የግንዛቤ መስጫ መድረኮች ግንዛቤያችንን አዳብረን ለማኅበረሰባችን የተሻለ የፍትሕ አገልግሎት እንድንሰጥ የሚያስችሉ በመሆኑ ተጠናክረው ቢቀጥሉ ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል። ተሳታፊዎቹ መድረኩን ላሰናዱ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት