የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕጻናት ቆረቆር በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል የተቀናጀ የማኅበረሰብ አቀፍ የምርምር ፕሮጀክት ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲው ከፍ ያለ በጀት የሚመደብለት 1.75 ሚሊየን ብር የበጀተለት የግራንድ ምርምር ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ዩኒቨርሲቲው 1.75 ሚሊየን ብር የበጀተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ መሳካትና ትግበራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡና ትብብራቸው እንዳይለይ አሳስበዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ኮርፖሬት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን ዘርዶ የቆሮቆር በሽታን አስመልክቶ ማኅበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ችግር ያለ መሆኑን ጠቁመው ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ከዚህ ጋር የተገናኙና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ ሲካሄድ ማኅበረሰቡን ያሳተፈና ያማከልለ መሆን ይገባዋል ያሉት ዶ/ር ዘሪሁን በተለይ በጸጉር ቤቶች ዘንድ የሚታዩ ችግሮች ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቆዳና አባላዘር ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የቆዳና አባላዘር በሽታ ስፔሻሊስት ሐኪምና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ምህረት ተጫኔ የሕጻናት ቆረቆር ፈንገስ በሽታ የሕጻናትን ጭንቅላት የሚያጠቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የ3 ዓመት ቆይታ ያለው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ምሕረት ከጥናት ባሻገር በጥናቱ ውጤት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ አቀፍ ትግበራ በት/ቤቶች፣ በጸጉር ቤትቶችና በጤና ተቋማት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በበሽታው ዙሪያ ከቀረበው መግለጫ ብዙ ግንዛቤ ያገኙ መሆናቸውን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡና ተናግረዋል፡፡ አክለውም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር እና የበሽታው ተጠቂ የሆኑ ሕጻናት ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከዞንና ከከተማ ጤና መዋቅሮች የተወጣጡ የበሽታ መከላከል የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን  አስተባባሪዎች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ ጤና ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት