በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት ንዑስ ፕሮጀክት ሁለት ከኮንሶና ጋርዱላ ዞኖች እንዲሁም ከገረሴ ወረዳ ለተወጣጡ የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር፣ የተፈጥሮ ጥበቃ፣ የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች እና ሞዴል አርሶ አደሮች ‹‹የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር በግብርና ዘርፍ›› በሚል ርእስ ከሰኔ 5-6/2017 ዓ/ም በኮንሶ ካራት ከተማ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ሥልጠናው የአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት ንዑስ ፕሮጀክት ሁለት መሪ በሆኑት ዶ/ር አሸናፊ ዱጉማ የሦስተኛ ዲግሪ የምርምር ውጤት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ሲሆን በሥልጠው 45 ሠልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡
ሥልጠናውን የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ያስጀመሩት የኮንሶ ዞን ግብርና ጽ/ቤት የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር አስተባባሪ አቶ ካሻይቶ ሰይሙሮ ሥልጠናው ወቅቱን የጠበቀ እና ከአደጋ እና ስጋት አስተዳደር አኳያ የሚስተዋሉ የአቅም ውስንነቶችን ከመቅረፍ አኳያ ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በአምዩ አይዩሲ ፕሮጀክት የንዑስ የፕሮጀክት ሁለት መሪና ዋና አሠልጣኝ ዶ/ር አሸናፊ ዱጉማ ዓለማችን በግብርናው ዘርፍ ብቻ በሚያጋጥሙ አደጋዎቸ የተነሣ በየዓመቱ 117 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምታጣ ተናግረው ጉዳቱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገራት የሚበረታ መሆኑንና ገጠራማው አካባቢ ደግሞ ሁለት ሦስተኛውን ጉዳት ወይም ኪሳራ ይሸከማል ብለዋል፡፡ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ አደጋዎች እና ስጋቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትም ሆነ በሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽእኖ በዓለምም ሆነ በሀገር ደረጃ እየጨመሩ መምጣታቸው በእጅጉ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አሸናፊ እነዚህን አደጋዎች እና ስጋቶች በተገቢ ሁኔታ ማስተዳደር ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በግብርና የሚተዳደረው የገጠሩ ማኅበረሰብ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ግጭት፣ የአንበጣ መንጋ፣ ወረርሽኝ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ አደጋዎችና ስጋቶች በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጠ በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ዋና ባለድርሻ አካላትን ማለትም የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር፣ የተፈጥሮ ጥበቃና የምግብ ዋስትና ባለሙያዎችን እንዲሁም የአርሶ አደሮችን አቅም መገንባት ለነገ የማይባል ጉዳይ በመሆኑ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ከዘርፉ ጽንሰ ሃሳብ ጀምሮ የስጋት አስተዳደር ስልቶች እና መዋቅራዊ አደረጃጃት እንዲሁም የፖሊሲ እና ስትራቴጂካዊ ማዕቀፎች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን ዶ/ር አሸናፊ ጠቅሰዋል፡፡ ሥልጠናው በዋናነት የቅድመ አደጋ እና ስጋት፣ የአደጋ ወቅት እና በድኅረ አደጋ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ የተሟሉ የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር አቅሞችን አማክሎ የተሰጠ መሆኑንም ዶ/ር አሸናፊ አውስተዋል፡፡
የአደጋ እና ስጋት ምንነትና ምንጮች፣ የአደጋ እና ስጋት መደባቸው፣ የአደጋ እና ስጋት መባባስ/አስከፊነትን የሚወስኑ ሁኔታዎች፣ የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር ስልቶች፣ ሀገር በቀል የአደጋ እና ስጋት አስተዳደር ስልቶች በተሰኙ ዋና ዋና ርእሶች ላይ ያተኮረው ሥልጠና በዶ/ር አሸናፊ ዱጉማ የተሰጠ ሲሆን ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ እንዲሁም አገራዊ የአደጋ እና ስጋት አመራር የፖሊሲ ማዕቀፍን የተመለከተው የሥልጠና ዋና ክፍል በዕጩ ዶ/ር ጥላሁን ሀብታሙ ተሰጥቷል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት