ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሽታና ድርቅን በመቋቋም ምርታማነትን መጨመር የሚያስችል የተሻሻለ የማሽላ ዝርያን ለማስተዋወቅ ያለመ የግራንድ ፕሮጀክት የሙከራ ማሳያ ምርምር የመስክ ምልከታ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ3 ወረዳዎች የመጡ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች በተገኙበት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ሰኔ 13/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ምርምሩ «Assessment of Community Perception towards Use of Sorghum Varieties and Climate Smart Agricultural Practices: Implications for Improving Sorghum Productivity in Selected Areas of Southern Ethiopia» በሚል ርእስ በተለይ በአርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ደራሼ እና ኮንሶ ካራት ዙሪያ ወረዳዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ በኮሌጁ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ት/ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ዋቅሹም ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዋቅሹም ምርምሩ የ1.75 ሚሊየን ብር ግራንድ ፕሮጀክት አካል ሲሆን ዓላማውም ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች የማሽላ ሰብሎችን የመጠቀም ሁኔታ፣ በቴክኖሎጂዎችና በተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎች ላይ ያላቸው ግንዛቤና አጠቃቀም እንዲሁም ማሽላን ከቦሎቄና ማሾ ሰብሎች ጋር አሰባጥሮ መዝራት ምርታማነትን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ የሚያመጣውን ለውጥ ማጥናት ነው፡፡ አየር በካይ የሆኑ ጋዞችን ለመቀነስ እና የአየር ንብረት ለውጥንና በሽታን ለመቋቋም ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎችና በተለይ ባልታረሱ የእርሻ መሬቶች ሰብሎችን አሰባጥሮ መዝራት «Climate Smart Agricultural Practice» ቴክኖሎጂዎች አስተዋጽአቸው የላቀ መሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የድኅረ ምረቃና ምርምር አስተባባሪና የግራንድ ፕሮጀክቱ ረዳት ተመራማሪ አግደው አበበ እንደገለጹት የኮሌጅ ግቢና የኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ ፉጩጫ ቀበሌ ለፕሮጀክቱ ምርምር ሙከራ ማሳያነት ተመርጠዋል፡፡ ዝናብ አጠር በሆኑ እንደ ደራሼ፣ ኮንሶና አርባ ምንጭ አካባቢዎች የመሬት እርጥበትን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን መጨመርና ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ እንደ ማሽላ ያሉ በምርምር የተገኙ የተሻሻሉ ሰብሎችን ለአርሶ አደሩና ለዘርፉ ባለሙያዎች ለማስተዋወቅ እንዲሁም ምርምሩ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት የመስክ ምልከታ መደረጉንም ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ 

በኮሌጁ የዕፅዋት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርና 3ኛ ዲግሪያቸውን በኮሌጁ እየተከታተሉ የሚገኙት የፕሮጀክቱ ተመራማሪ ዘሪሁን ስንታ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ፣ በትንሽ መሬት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአፈር ለምነትን የሚጠብቁና በሽታን የሚቋቋሙ ሰብሎችን መፍጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማልማት የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመስክ ምልከታው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ የገጠር ልማት የግብርና ኤክስቴንሽን ትም/ት ክፍል መምህራንና ተመራማሪዎች፣ ምርምሩ ከሚደረግባቸው ቀበሌያት የተወጣጡ አርሶአደሮችና ባለሙያዎችና ተገኝተዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት