አርባ ምንጭ  ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ እና  ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሀገሪቱ 8ኛውን የመድኃኒት ደኅንነት መከታተያና ማስተባበሪያ ማዕከል  ሰኔ 17/2017 ዓ.ም በይፋ ሥራ አስጀምሯል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ እንደገለጹት የማዕከሉ በሆስፒታሉ መክፈት ከመድኃኒቶች ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በጊዜ መፍትሔ እንዲያገኙ ያግዛል፡፡ ማዕከሉ በአርባ ምንጭና አካባቢው ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዶ/ር ደስታ ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተወካይ እና የመድኃኒት አምራቾች ኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈጸም መሪ ሥራ አሰፈጻሚ አቶ ጌታቸው ገነቴ መድኃኒቶች ጎጂ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ የጤና ባለሙያዎችና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል። የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ባለሥልጣኑ ቁልፍ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እና በመምረጥ የመድኃኒት ደኀንነትና ክትትል ማስተባበሪያ ማዕከላትን እያቋቋመ እንደሚገኝ ያስረዱት ተወካዩ በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል የተከፈተው ማዕከል ስምንተኛው መሆኑንም አመላክተዋል። 

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኮንን ቶንቼ ማዕከሉ በመከፈቱ ባለሥልጣን መ/ቤቱን  አመስግነው የማዕከሉ መከፈት ለአካባቢው መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።  በቀጣይም የዞኑ መንግሥት ከማዕከሉ  ጋር በቅርበት እንደሚሠራም አቶ መኮንን አክለዋል።

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርትና አገልግሎት ም/ዳይሬክተርና የማዕከሉ ተጠሪ አቶ ጌታሁን አስማማው የማዕከሉን  መከፈት  አስመልክቶ ለ2 ቀናት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በአካባቢው ካሉ መዋቅሮች ለተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል። የተከፈተው ማዕከል የደቡብ ኢትዮጵያ የመድኃኒቶች ደኅንነት መከታተያ ማስተባበሪያ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ማዕከሉ በክልሉ ካሉ ጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡

ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋርም በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባባቢያ ሰነድ መፈረሙንም አቶ ጌታሁን ገልጸዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት