አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአዩዳ ኢን አክስዩን ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት እና ከስፓኒሽ ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የሞሪንጋ ተክል ላይ በጋራ የሚሰራ የትብብር ፕሮጀክት ለማስጀመር በምዕራብ አባያ ወረዳ ዶሼ ቀበሌ እና በወላይታ ዞን አባላ አባያ በተሰኙ በተመረጡ ስፍራዎች የምሪንጋ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ምሪንጋ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ተክል ሲሆን ፕሮጀክቱ የገበያ ትስስርን በማስፋት በደቡብ ብቻ ይታወቅ የነበረውን የሞሪንጋ ተክል በመላ ሀገሪቱ እንዲታወቅ ጉልህ አስተዋጾ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የሞሪንጋን ችግኝ መትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያወሱት ፕሬዝደንቱ ለምግብነት ካለው ሚና ባሻገር ለመድኃኒትነትና አረንጓዴ አሻራ ሥራ ጉልህ አስተዋጽኣ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የችግኝ ተከላው በ3 ወረዳዎች ላይ 90 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚከናወን ገልጸው ሥራው ለአንድ ዓመት የሚቆይ 61 ሚሊየን ብር የተበጀተለትና ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ሞሪንጋ ለተለያየ አገልግሎት እንደሚውል የገለጹት ዶ/ር ተክሉ የተለያዩ ጥናቶች በዘርፉ እየተከናወኑ መሆኑንም አመላክተዋል። ዶ/ር ተክሉ ሞሪንጋ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኝ፣ ህብረተሰቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ለወጣቶች እንዲሁም ለሴቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ጭምር አስረድተዋል።
የአዩዳ ኢን አክስዩን የደቡብ አከባቢ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ሞንጃሬ የሞሪንጋ ፕሮጀክት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችና ጽ/ቤቶች ጋር በጋራ ተቀርፆ እየተሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የፕሮጀክቱ በጀት ከስፔን መንግስት ተራድኦ ድርጅት የተገኘ መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪው ፕሮጀክቱ በጋሞና ወላይታ ዞኖች በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኪንዶ ኮይሻ ላይ ከተክሉ ዘይት የማምረት ተግባር መጀመሩን የገለጹት አስተባባሪው ከዛም ልምድ በመቀመር በሌሎች ሥፍራዎች ተሞክሮውን ለማስቀጠል መታስቡን አስረድተዋል፡፡ የዘይት ምርቱን በማምረት ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንዳለ የገለጹት አቶ ዳንኤል ቆመር የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት እና ሌሎች ተጨማሪ ተባባሪ አካላትን በማሳተፍ የገበያ ሰንሰለቱን ለማሳለጥ ስምምነት ላይ መደረሱን አመላክተዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንሰት ላይ ያለውን ልምድ ወደ ሞሪንጋ ለማስፋት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ቀድሞ ሞሪንጋ ላይ እየተሰራ ያለውን ሥራ እሴቱን ከፍ በማድረግ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ ታልሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በችግኝ ጣቢያዎች ችግኞችን ከማምረት ጀምሮ አነስተኛ ፋብሪካዎችን በመገንባት ሞሪንጋን የማቀነባበር ሥራም በቀጣይ እንደሚሰራ ዶ/ር አዲሱ ገልጸዋል፡፡ ቴክኒካል ድጋፎችን ጨምሮ ሌሎች የድጋፍ ሥራዎችም ዩኒቨርስቲው እንደሚያደርግ ዶ/ር አዲሱ አመላክተዋል፡፡
በምዕራብ አባያ ወረዳ የኮሎ ሁለገብ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ወንጄ ወጋሶ ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይዞ የመጣ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው በፕሮጀክቱ የታለመውን ግብ ለማሳካት እንደሚተጉ ተናግረዋል።
For more Information Follow us on:-
Website - https://www.amu.edu.et/
Telegram - https://t.me/arbaminch_university
Facebook - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
YouTube - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
Public and International Relations Executive