በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ተመራማሪዎች በተገኙበት በኮሌጁ በእንስሳትና እጽዋት ሳይንስ ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምር ሥራዎች የመስክ ምልከታ ዛሬ ነሐሴ 22/2017 / ተካሂዷል፡፡

የምርምርና ትብብር /ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ / ተክሉ ወጋየሁ በኮሌጁ በእንስሳትና ዓሣ እንዲሁም አጽዋት ሳይንስ ዘርፎች የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችና ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የመስክ ምልከታው በዋናነት በኮሌጁ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ድክመትና ጥንካሬዎችን በመለየት  ለተሻለ ሥራ የሚሆኑ አስፈላጊ ድጋፎችን ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግዋል፡፡ በኮሌጁ ዘመናዊ የከብቶች በረት ያለ መሆኑ ትለቅ ዕድል ነው ያሉት / ተክሉ ይህን ኃብት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ማስገባትና ከምርምር ባሻገር ለዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ የገቢ አማራጭ እንዲሆን መስራት  ይገባል ብለዋል፡፡ ዓሣን በቀላሉ በቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ በሚዘጋጁ ትንንሽ ገንዳዎች ማራባትና ለምግብነት መጠቀም እንደሚቻል ለማሳየት በኮሌጁ የተጀመረው ሥራ  መስፋት የሚገባውና ለማኅበረሰቡም በቶሎ ሊሸጋገር የሚችል ተግባር መሆኑን የገለጹት /ፕሬዝደንቱ ይህም በሂደት በጫሞና አባያ ሐይቆች ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ረገድ የራሱን ሚና ሊጫወት የሚችል ነው ብለዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምር ውጤቶችን ወደ ገቢ የመቀየር ጉዳይ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ለሚሰራ ተቋም የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት / ተክሉ በዚህ ረገድ የግብርናው ዘርፍ ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በኮሌጁ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ መሰል የምርምር የመስክ ምልከታ ቀኖች የምርምር ውጤቶች በተግባር የሚታዩባቸው፣ አዳዲስ አሠራሮች የሚተዋወቁባቸው እንደመሆናቸው ሌሎች በላድርሻ አካላትን ባሳተፈ መንገድ በሌሎች ኮሌጆች ጭምር ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ / ተክሉ አውስተዋል። እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳይ ከመማር ማስተማር ሥራዎች እኩል በየኮሌጁ የሚገኙ አካዳሚክ ካውንስሎች አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት / ተክሉ በዚህም በየኮሌጅ የሚገኙ የምርምር ማዕከላት ዳይሬክተሮችን የአካዳሚክ ካውንስል አባል ማድረግ በዘርፉ ይበልጥ ለመላቅ ትልቅ ሚና እንደሚኖርው አስምረዋል።

የአስተዳደርና ልማት /ፕሬዝደንት / ጳውሎስ ታደሰ በምልከታቸው በኮሌጁ እየተሰሩ የሚገኙ የመስክ ምርምር ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን መስክረዋል፡። በኮሎጁ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሁም ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  ያሉ ጅምር ሥራዎችን ለማስፋት የሚረዱ አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንደሚደረግ ያረጋገጡት / ጳውሎስ የኮሌጁ መምህራንና ተመራማሪዎች ዘንድ ያለው መነሳሳትና ትብብር ይበልጥ መጠናከር እንዳለበትም መክረዋል።

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን / ደግፌ አሰፋ የምርምር የመስክ ቀንን በማስመልከት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በኮሌጁ የተካሔደው የመስክ ምልከታ እንደ ኮሌጅ ያሉንን አበረታች እንቅስቃሴዎች በተግባር ለማሳየት እንዲሁም የገጠሙን ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ከፍተኛ አመራሩ የበኩሉን እንዲያደርግ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል። አመራሮቹ በእንስሳት፣ አሣ እንዲሁም የተለያዩ እጽዋቶች ላይ የሚደረጉ የምርምር ሰርቶ ማሳያ ሥራዎችን በአካል ማየታቸው በቀጣይ ሥራዎቹ  ሰፍተው የአካባቢውን ማኀበረሰብ የሚጠቀሙ እንዲሁም የተቋሙን የምርምር ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።  ኮሌጁ በግብርናው ዘርፍ ለአርሶአደሮች ሞዴል፣ ለመንግስት የፖሊሲ ግብአቶችን የሚያቀርብ፣ ምርጥ ዘሮች የሚወጡበት የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽዖ የሚያደርግ የላቀ ተቋም ለመሆን እየሰራ መሆኑን የገለጹት / ደግፌ ኮሌጁ በደንብ ከተደገፈና ያሉ አቅሞችን አሟጦ መስራት ከተቻለ እስከ 10 ከመቶ የሚሆነውን የዩኒቨርሲቲውን በጀት መሸፈን ይችላልም ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከል ዳይሬክተር አቶ እሳቱ በቀለ ማእከሉ በወተትና ስጋ  ላሞች፣ የሥጋና እንቁላል ጣይ ዶሮዎች፣ ዓሣ፣ ሌሎችም ላይ ዝርያ የማሻሻል፣ ጤና እና የእንስሳት መኖ ማሻሻያ ላይ ትኩረት ያደረጉና  ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ  የምርምር ፕሮጀክቶችን እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ በሁሉም ዘርፎች የጀመራቸውን ሥራዎች የማስፈትና የምርምር ውጤቶችን ወደ ገበያ በማቅረብ ዩኒቨርሲቲውን በገቢ ደረጃ የማገዝ ዕቅድ ያለው መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ለዕቅዱ ስኬት አስፈላጊ ግብአቶችን መሟላት ወሳኝ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው አመራር በልዩ ሁኔታ ለማዕከሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ