ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ ከአባታቸው አቶ ሽብሩ ጨጨ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አምኔ ጎሌ በቀደሞው ጋሞ አውራጃ በኦቾሎ ቀበሌ ግንቦት 29/1960 ዓ/ም ተወለዱ፡፡ ዶ/ር ስምዖን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በላንቴ 1ኛ ደረጃና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ ዶ/ር ስምዖን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ የትምህርት መስክ ሐምሌ 3/1984 ዓ/ም፣ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ ሐምሌ 2/1991 ዓ/ም እንዲሁም የ3ኛ ዲግሪያቸውን ቤልጂየም ሀገር ከሚገኘው አንተወርፕ ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ የካቲት 25/2016 በ ‹‹Terrestrial Ecology›› የትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ከ1985-1991 ዓ/ም ድረስ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በአርባ ምንጭ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በመምህርነት፣ ከ1992-1996 በጂቲዜድ ፕሮጀክት ባለሙያ በመሆን የሰሩት ዶ/ር ስምዖን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ነሐሴ 24/1996 ዓ/ም ተቀላቅለዋል፡፡ ከመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራቸው ባሻገር በተለያዩ የኃላፊነት መስኮች ዩኒቨርሲቲውን ያገለገሉት ዶ/ር ስምዖን ከሐምሌ 1/1997-መጋቢት 1/1999 ዓ/ም የተከታታይ ትምህርት ማስተባበሪያ ኃላፊ፣ ከግንቦት 19/2000 ዓ/ም-ሐምሌ 19/2001 ዓ/ም የጥናት፣ ምርምርና ሕትመት ማስተባበሪያ ኃላፊ፣ ከሐምሌ 20/2001 ዓ/ም- ጥር 8/2004 ዓ/ም የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት፣ ከግንቦት 23/2008 ዓ/ም- ሕዳር 9/2010 ዓ/ም የምርምር ዳይሬክተር፣ ከሕዳር 10/2010- ጥር 30/2013 ዓ/ም ድረስ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት በመሆን ዩኒቨርሲቲውን አገልግለዋል፡፡
ከነሐሴ 25/2012 ዓ/ም ጀምሮ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ ያገኙት ዶ/ር ስምዖን ከግንቦት 20/2017 ዓ/ም ጀምሮ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን በመሆን ሕይታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር ስምዖን ባለትዳርና የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ 57 ዓመታቸው ነሐሴ 30/2017 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዶ/ር ስምዖን ሽብሩ ኅልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ጓደኞችና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ይመኛል፡፡
የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ነገ ቅዳሜ ጳጉሜ 1/2017 ዓ/ም በ8 ሰዓት በአርባ ምንጭ መድኃኒዓለም ካቴድራል የሚፈጸም ይሆናል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት