የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት በሥሩ ለሚገኙ ከሁሉም ካምፓሶች ለተወጣጡ አዲስ ባለሙያዎች ከነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት የቆየ የቢሮ ማሽኖች እና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ጥገና ላይ ያተኮረ የአቅም ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢያሱ ዲላ የሥልጠናው ዓለማ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች ዳይሬክቶሬቱን ለተቀላቀሉ አዲስ ባለሙያዎች የቢሮ ማሽኖችን እና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መጠገን የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሥልጠናው የመጀመሪያ ዙር መሆኑንና ቀጣይነት እንዳለው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ሠልጣኞቹ በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች በተግባር ማሳየት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ጥገና ክፍል ቡድን መሪ አቶ ሚልኪያስ በላይ ሠልጣኞቹ ለረዥም ጊዜ ከኮምፕዩተር አጠቃቀም ርቀው የቆዩ ስለሆነ ልምድ ባላቸው አሠልጣኛች ከመደበኛ የኮምፕዩተር አክሰሰሪ ጀምሮ እስከ ብልሽት ጥገና ድረስ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ ሲስተም አድሚኒስትሬተር የሆኑት አሠልጣኝ ተመስገን ጎሎ በበኩላቸው ሠልጣኞቹ መሠረታዊ የኮምፕዩተር ሶፍትዌር አጠቃቀም እንዲሁም የኮፒ ማሽንና ፕሪንተር የመሳሰሉ የቢሮ ማሽኖች በመጠገን መጠቀም የሚያስችላቸውን በቂ ክሂሎት ያገኙበት ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡
የኩልፎ እና ጫሞ ካምፓስ የመረጃና መገናኛ ቴክሎጂ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ዓለሚቱ ኢባዳ እና ወ/ሪት ዘነበች ሰዳ ሥልጠናው በጣም አስፈላጊ አና ለሥራ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ የቢሮ ማሽኖችን መጠገን የሚያስችል ዕውቀት ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት