የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይነስ ኮሌጅ በወሊድ ጊዜ የጨቅላ ሕፃናት መታፈንን ለመቀነስ እንዲሁም የጡት ማጥባት ልምምድን በማሻሻል የጨቅላ ሕፃናት የኢንፌክሽን ተጋላጭነትና የሰውነት ሙቀት መቀነስን ለመከላከል ያለሙ ሁለት የትብብር ፕሮጀክቶችን ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነሐሴ 30/2017 ዓ/ም በይፋ አስጀምሯል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በዩኒቨርሲቲው በውስጥ በጀትና በትብብር በርካታ ምርምሮችና ፕሮጀክቶች የሚሠሩ መሆኑን ጠቅሰው በትብብር ፕሮጀክቶች ረገድ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሰፊ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ በተመራማሪዎች ጥረት የሚመጡ የትበብር ፕሮጀክቶችን በልዩ ሁኔታ እናበረታታለን ያሉት ዳይሬክተሩ ይፋ ለተደረጉት ፕሮጀክቶች ስኬት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ በኮሌጁ ካሉ 10 የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች አንዱ የሆነው ሚድዋይፍሪ ከመማር ማስተማር ባሻገር ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ ፕሮግራሙ በያዝነው ዓመት ሀገር አቀፍ ዕውቅና ካገኙ ሁለት ፕሮግራሞች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ዘርይሁን ይፋ የተደረጉት ፕሮጀክቶች በጤና ተቋማት የሚገጥሙ የጨቅላ ሕፃናት ችግሮችን ተደራሽ በማድረግ ተጨባጭ መፍትሔ ለማምጣት የሚረዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹Integral Simulation-Based Training and Clinical Mentorship to Reduce Perinatal Asphyxia through Improved Assisted Vacuum Delivery and Neonatal Resuscitation Skills in Ethiopia›› በሚል ርእስ የሚሠራው ፕሮጀክት የጨቅላ ሕፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን በወሊድ ጊዜ መታፈን ለመቀነስ በማለም የሚሠራ መሆኑን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚድዋይፍሪ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ ሥዩም ገልጸዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ በወሊድ ጊዜ በመታፈን የሚሞቱ ጨቅላ ሕፃናት ቁጥር በዓመት 4 ሚሊየን የሚደርስ ሲሆን በሀገራችን ከሚወለዱ 1ሺህ ሕፃናት 27ቱ በዚሁ ምክንያት ይሞታሉ፡፡ መንግሥት ይህንን ቁጥር በመቀነስ እ.ኤ.አ በ2030 ወደ 12 ለማድረስ ማቀዱን የጠቆሙት ዶ/ር መለሰ ይህን ለማሳካት መሰል የምርምር ፕሮጀክቶችን በመተግበር ምሁራንና ተመራማሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በኮሌጁ የሚገኘው የአርባ ምንጭ የሥነ ሕዝብና የጤና ምርምር ማእከል በመረጃ ማሰባሰብ ሒደት ከሚያካትታቸው አርባ ምንጭ እና በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተመረጡ ሦስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የመለማመጃ ማእከላት በማደራጀት ባለሙያዎች በስልክ መተግበሪያ በታገዙ ዘመናዊ መለማመጃዎች/Laerdal Simulator dolls/ እንዲሠለጥኑ ይደረጋል፡፡ በዚህም ባለሙያዎቹ በሚያዋልዱበት ሰዓት በመሣሪያ በማገዝ እናቶች ቶሎ እንዲወልዱና የሕፃናት መታፈን እንዲቀንስ እንዲሁም የመታፈን ችግር ከገጠመም ሕፃናቱ በቶሎ እርዳታ አግኝተው ሕይወታቸውን መታደግ እንዲቻል የሚሠራ መሆኑን ዶ/ር መለሰ አብራተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመታት እንደሚቆይና አስፈላጊው የገንብ ድጋፍ ከ‹‹Laerdar Foundation›› የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው የምርምር ፕሮጀክት የዩኒቨርሲቲው ሕክምና ት/ቤት መምህርና የሕፃናት ስፔሻሊስት ሐኪም በሆኑት ዶ/ር አብነት ታከለ የቀረበ ሲሆን ‹‹Effect of Integral Support program on Breastfeeding Practices to Reduce Neonatal Hypothermia and Sepsis among Post-Cesarean Mothers in Southern Ethiopia›› በሚል ርእስ የሚሠራ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እናቶች የጤና ባለሙያዎችን ምክርና ድጋፍ አግኝተው የጡት ማጥባት ልምዳቸውን በማሻሻል የጨቅላ ሕፃናት የሰውነት ሙቀት መቀነስና የኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያለመ መሆኑን ዶ/ር አብነት ተናግረዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው በዓለማችን 2.4 ሚሊየን ጨቅላ ሕፃናት አንድ ወር ሳይሞላቸው የሚሞቱ ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት ከተቀመጡ ነገሮች ዋነኞቹ ኢንፌክሽን እና የሰውነት ሙቀት መቀነስ ናቸው፡፡ ጨቅላ ሕፃናት በተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ የጡት ወተት እንዲያገኙ ማድረግ ችግሩን ለመቀነስ የሚረዳ ቢሆንም በተለይም በኦፕሬሽን ከወለዱ በኋላ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት የሚያጠቡ እናች ከ35 በመቶ በታች ናቸው፡፡ በ‹‹Nestle Foundation›› የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ ከአርባ ምንጭ፣ ጎንደር፣ ሐዋሳ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ ተመራማሪዎች የሚተገበረው የትብብር ፕሮጀክት እናቶች በቂ ዕውቀት አግኝተው በወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ማጥባት እንዲጀምሩ በማገዝ የጨቅላ ሕፃናት የሰውነት ሙቀት መቀነስና ኢንፌክሽንን በመከላከል የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ይሠራል ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ከተለያዩ የጤና ተቋማትና ባለድርሻ ሴክተሮች የመጡ ተሳታፊዎች በፕሮጀክቶቹ መጀመር የተሰማቸውን ደስታና ምስጋና ገልጸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት