በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት አዘጋጅነት ‹‹የምርምር፣ የፕሮጀክት እና የኅትመት ስኬቶች›› በሚል መሪ ቃል መስከረም 24/2017 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክት እና የኅትመት ቀን የተከበረ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት በፕሮጀክት፣ በምርምርና ኅትመት ዘርፍ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ኮሌጆች፣ ተመራማሪዎች እና ግለሰቦች ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የማኅበረሰቡን ችግሮች ለሚፈቱ ምርምሮች ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ የቆየ ሲሆን የጥናትና ምርምር ውጤቶቹ ዕውቅና ባላቸው ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እየታተሙ ነው፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት ቁጥሩን ከነበረው ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ያመለከቱት ፕሬዝደንቱ በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክት እና የኅትመት ቀን መከበሩ ምርምሮች ሸልፍ ላይ ከመቀመጥ ባለፈ ወደ ተግባር ወርደው የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ የሚያነሣሣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሠሯቸው ምርምሮች የሚለኩ ሲሆን በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥምርታ ለሚሠሩ የምርምር ሥራዎችና ተመራማሪዎች ዕውቅና መስጠት ዩኒቨርሲቲው በምርምር ረገድ ላቀደው ስኬት እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው በጠንካራ ምርምር እና ልማት መካከል ያለውን ወሳኝ ግንኙነት በማውሳት ዓለም አቀፋዊ መለኪያዎችን ለማሟላት ለጥራት ደረጃዎች ቅድሚያ መስጠት እንዲሁም ተከታታይ ክትትል እና ትብብር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ አክለውም የምርምር ሥራ የረዥም ጊዜ ጥረትንና ትጋትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይገባዋል፤ የዛሬው ውጤታችንም የዚሁ የረዥም ጊዜ ጥረታችንና ትብብራችን ውጤት ነው ብለዋል፡፡ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስተዋፅዖ ላበረከቱ ሁሉ ም/ፕሬዝደንቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ኅትመት እና ግራንት ማኔጅመንት ወቅታዊ አቋምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በኅትመት ስነዳና ሥርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምዖን ደርኬ እና የግራንት እና የትብብር ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ኃይሉ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም በሁለቱም ዘርፎች የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን በዘርፉ ዕውቅና ያላቸው ተመራማሪዎች ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ በ2017 በጀት ዓመት በፕሮጀክት፣ በምርምርና ኅትመት ዘርፍ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ኮሌጆች፣ ተመራማሪዎች እና ግለሰቦች ሽልማትና ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በድምር ኅትመቶች እና ስኬታማ የግራንት ፕሮጀክቶች ላይ ለነበረው የላቀ አበርክቶ ዕውቅና አግኝቷል። በኅትመት ዘርፍ ዶ/ር ይልቃል ታደለ፣ ዶ/ር አበራ ኡንቻ እና ዶ/ር ንጉሤ ቦቲ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሦስተኛ ሲወጡ በምርምር ግራንት ፕሮጀክት ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ፣ ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እና ዶ/ር አሸናፊ ኃይሉ በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከተሸላሚዎች መካከል ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የዓመቱ ምርጥ ግራንት ፕሮጀክት ዘርፍ አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ባገኙት ዕውቅና መደሰታቸውንና የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸው ሽልማቱ በቀጣይ ለበለጠ ስኬት እንዲተጉ የሚያበረታታና ሌሎችንም የሚያነሣሣ መሆኑ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን ለዩኒቨርሲቲውና መርሐ ግብሩን ላስተባበሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማራዎች፣ የሴኔት አባላት፣ የአስተዳደር ዘርፍ ሠራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት