በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት አዘጋጅነት መስከረም 22/2018 ዓ/ም የአስተዳደር ሠራተኞች ፎረም ውይይት ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ፕ/ር ጳውሎስ ታደሰ ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲው መምህራን ፎረም መኖሩን አስታውሰው ሁሉንም የአስተዳደር ሠራተኞች የሚያሳትፍና በዕቅድ የተመራ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የዩኒቨርሲቲውን ተልእኮና ራእይ እውን ለማድረግ የአስተዳዳር ሠራተኞች ፎረም መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡ የፎረሙ ምሥረታ በዕቅድ ለመመራት፣ የአስተዳደር ሠራተኞችን በራስ የመወሰን አቅም ለማሳደግ፣ በሁሉም የሥራ ክፍሎች እኩል አፈጻጸም አንዲኖር እንዲሁም ለሚያጋጥሙ ችግሮች ወጥ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚረዳ ፕ/ር ጳውሎስ ተናግረዋል፡፡
አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በሳምንት ቢያንስ 39 ሰዓት የመስራት ግዴታ አለበት ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ከሰዓት አጠቃቀም ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አዲስ የሥራ ሰዓት አጠቃቀም የውስጥ መምሪያ ተዘጋጅቶ ከጥቅምት 1/2018 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር አውስተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ተልእኮ ለማሳካት ሁሉም ሥራ ክፍሎች የራሳቸው የሥራ ዕቅድ ኖሯቸው ከከፍተኛ ሠራተኛ ጀምሮ ሳምንታዊ ዕቅድ ማቀድ፣ በዕቅዱ መሠረት ውጤታማ ሥራ መሥራት እና በአፈጻጸማቸው መሠረት ውጤት መስጠት እንደሚጠበቅ የገለጹት ፕ/ር ጳውሎስ ለዚህም የሥራ ክፍል ኃላፊዎች በበላይነት መቆጣጠር የሚኖርባቸው ሲሆን በየ15 ቀናት ከሠራተኞች ጋር ውይይት እንዲደረግ የጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎችና አስተባባሪዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት