የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጋሞና ጎፋ ዞኖች ተላላፊ ላልሆነ ዝሆኔ ሕክምና ተግዳሮት የሆነውን ቁርጭብት /Nodulectomy/ በቀዶ ጥገና ማስወገድ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ፕሮጀክት በርካቶችን ከእግር መቆረጥ፣ መገለል እና ከሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየታደገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ጥቅምት 29/2018 ዓ/ም በዚሁ ፕሮጀክት አማካይኝት በበሽታው ላለፉት 8 ዓመታት ሲሰቃዩና እግራቸው እንዲቆረጥ በማኅበራዊ ሚዲያ እርዳታ ሲሰበሸብላቸው ለነበሩ ግለሰብ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምኘርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳና የአባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ሐኪም በሆኑት በፕሮፌሰር ወንድማገኝ እንቢያለ እና የፕላስቲክ ሰርጀሪ ስፔሻሊስት በሆኑት በዶ/ር ደስታ ጋልቻ የተመራ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷቸው እግራቸውን ከመቆረጥ መታደግ ተችሏል፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በኮሌጁ በርካታ የማኅበረሰቡን የጤና ችግሮች የሚፈቱ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው በኮሌጁ የሚገኘው ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ጭምር በመተባባር የሚተገብራቸውን ሥራዎች ለአብነት አንሥተዋል፡፡
በዝሆኔ በሽታ ሳቢያ የሚከሰተውን እብጠት በቀዶ ሕክምና ማስወገድ እንደ ሀገር የተለመደ ሕክምና አለመሆኑን ያነሱት ዶ/ር ደስታ በዚህ የትብብር ፕሮጀክት የቀዶ ሕክምናውን ባገኘኙ ሕሙማን ላይ የታየው ለውጥ ሕክምናውን እንደ ሀገር ማስፋት እንደሚገባ ያመለከተ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አንድ የሕክምና ባለሙያ በዚህ በጎ ሥራ ላይ መሳተፈቸው በእጅጉ እንደሚያስደስታቸው የገለጹት ዶ/ር ደስታ በቀጣይም ሥራውን በሌሎች አካባቢዎች ለማዳረስ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ እንደ ኃላፊም ሆነ እንደ ባለሙያ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቆዳና የአባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ሐኪምና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እንቢያለ ኢትዮጵያ ውስጥ 1.5 ሚሊየን የሚሆኑ ስዎች ተላላፊ ባልሆነ የዝሆኔ በሽታ የተጠቁ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 30 ከመቶ ያህሉ በእግራቸው ላይ በሚፈጠር እብጠት (ቁርጭብት) ምክንያት ለበርካታ የጤናና ማኅበራዊ ችግሮች የሚዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂዎች በሕክምና መስጫ ማዕከላት ባለ የተሳሳተ አረዳድ ምክንያት ተገቢውን ሕክምና እያገኙ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰሩ የተደረጉ ጥናቶችና በሙከራ ፕሮጀክቱ የታዩ ለውጦች ግን ሕሙማንን በቀላል ቀዶ ሕክምና ከችግሩ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚቻል አሳይቷል ብለዋል፡፡
የሕክምና ባለሙያዎች በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቀዶ ጥገና ከተደረጉ ቁስላቸው አይድንም በሚል እሳቤ እግራቸው እንዲቆርጥ እንደሚያደርጉ ያነሡት ፕ/ር ወንድማገኝ በዚህ ፕሮጀክት በጤና ጣቢያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን በማሠልጠን ብቻ ያለ ቀዶ ጥገና ሐኪም በርካታ ሕሙማንን ከስቃይ መታደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ሥራውን በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትና በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ዋና ተመራማሪው አክለዋል፡፡
ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የምርምር ማዕከሉ ከተመሠረተ 10 ዓመት እንደሆነው ገልጸው የማዕከሉ የሥራ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና ከአካባቢ አልፎ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በማዕከሉ ተግባራዊ እየሆኑ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ተላላፊ ያልሆነ የዝሆኔ በሽታን በተመለከተ በጤና ጣቢያዎች የሚገኙ ባለሙያዎችን በማሠልጠን እየተሰጠ የሚገኘው የቀዶ ሕክምና ሥራ አንዱ መሆኑን ያነሡት ዳይሬክተሩ እስከ አሁን ባለው የሥራ ሂደት 84 ሕሙማን አገልግሎቱን አግኝተው ጤናማ ሕይወት መምራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ተባባሪ ተመራማሪ ዓለማየሁ በቀለ እንደገለጹት የዝሆኔ በሽታ በዓለም ጤና ድርጅት ከተለዩ 22 የተዘነጉ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች መካከል አንዱ ሲሆን በሽታው ተላለፊና ተላላፊ ያልሆነ ዝሆኔ በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ የትብብር ፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት በሀገራችን በስፋት በሚገኘው ተላላፊ ባልሆነ ዝሆኔ ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዓለማየሁ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ከሚገጥማቸው የጤና ችግር ባሻገር በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የመገለል ችግር በሰፊው የሚደርስባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተላላፊ ያልሆነ ዝሆኔን በማከም ሒደት ውስጥ በበሽታው የተጠቃን እግር መቁረጥ እንደ መፍትሔ ሲታይ ቆይቷል ያሉት አስተባባሪው በዚህ ፕሮጀክት 84 የሚሆኑ ሕሙማን በአማካይ በ21 ቀናት ውስጥ ብቻ በተደረገላቸው ቀዶ ሕክምና ድነው ጫማ መጫማትና ማኅበረሰቡን መቀላቀል ችለዋል ብለዋል፡፡ በዛሬው ዕለት በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል የቀደ ጥገና ሕክምና አገልግሎት ያገኘው ታካሚ የዚሁ ችግር ተጠቂና በማኅበራዊ ሚዲያ እግሩን ማስቆረጥ እንዲቻል ገንዘብ ሲዋጣለት የነበረ ግለሰብ ሲሆን በተደረገለት ሕክምና እግሩን ከመቆረጥ ማዳን እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚያከናውናቸው የበጎ ተግባር ሥራዎች የሚታወቀው ማስተር አብነት ከበደ ከታካሚው ጋር በአጋጣሚ እንደተገናኘ ገልጾ በግለሰቡ ጉዳይ በብዙ የሕክምና ባለሙያዎች የተሰጠው መፍትሔ እግር መቁረጥ በመሆኑ ለዚሁ ሕክምና የሚሆን ገንዘብ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያሰባስብበት ወቅት የግለስቡን ችግር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በቀዶ ሕክምና ማዳን እንደሚቻል ጥቆማ እንደደረሰው ተናግሯል፡፡ በጥቆማው መሠረት በአርባ ምንጭ ተገኝተን የወንድማችንን እግር ከመቆረጥ ታድገናል ሲል ማስተር አብነት ተናግሯል፡፡ ይህ ሕክምና መኖሩ በሀገራችን ብዙም አይታወቅም ያለው ማስተር አብነት አገልግሎቱን በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እንዲሠራ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የትብብር ሥራው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች የምርምር እና ሥልጠና ማዕከል፣ ‹‹NaPAN›› እና ‹‹International League of Dermatological Societies (#ILDS)›› የተሰኙ ድርጅቶች፣ ጤና ሚንስቴር እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ ነው፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

