የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ለሕክምና ባለሙያዎች የሚውሉ የበሽታ መከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ታኅሳስ 9/2018 ዓ/ም አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ከወቅታዊ ችግር ጋር ተያይዞ በተለይ የሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከበሽታዉ ተከላክለው ማህበረሰቡንም መደገፍ እንዲችሉ ለማድረግ የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ዩኒቨርስቲው በቀጣይ ጊዜያት መሰል ድጋፎችን እንደሚያደርግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚተጋ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር እንዳሻዉ ሽብሩ እንደገለጹት የማርበርግ በሽታ በንክኪ የሚተላለፍ በመሆኑ በትራንስፖርት አገልግሎት እና በማህበራዊ ግንኙነት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። የሕክምና ባለሙያዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ከማከማቸዉ በፊት በሽታዉን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶችን በአግባቡ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ገልጸው የበሽታውን ምልክቶች ማወቅ እና ንክኪ ያላቸዉን ወደ ህክምና ማዕከል ሳይዘገዩ ማምጣት ፋይዳው የጎላ መሆንን ገልጸዋል። በአርባ ምንጭ፣ በሶዶ እና ሳውላ ከተሞች ለይቶ ማቆያ ማዕከላት መቋቋማቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የቁሳቁስ ድጋፍ ላደረገው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ጤና ቢሮ ስም ምሥጋና አቅርበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የቁሳቁስ ድጋፉ በዋናነት ወቅታዊ ጉዳዩን ታሳቢ በማድረግ በጤና ተቋማት ለተቋቋሙ ለይቶ ማቆያ ማዕከላት የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በሰዎች ላይ የተከሰተው እ.ኤ.አ. በ 1967 በጀርመን ሀገር ማርበርግ ከተማ ሲሆን በአፍሪካም በተለያዩ ሀገራት ማለትም ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ አንጎላ እና ጋና ተከስቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ማህበረሰባችን በሽታው የሚተላለፍባቸውን መንገዶች በአግባቡ ተረድተው እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ከበሽታው ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም መሰል የቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቨ ዳይሬክተር ዶ/ር ደሰታ ጋልቻ ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የተደረገው ድጋፍ ተቋማት አብሮ መስራትንና መተባበርን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሰርጅካል ፌስ ማስክ ፣ ኤግዛሚነሽን ግላቭ ፣ ሙሉ በሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን (Protective Cover)፣ ፌስ ሺልድ፣ ሳኒታይዘር በድጋፍ የተሰጡ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ዶ/ር ደስታ ገልጸዋል።
የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አምባቸዉ ዱማ በበኩላቸዉ ድጋፉ ለወቅታዊው ችግር በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ከሆሰፒታል ጋራ አብሮ እንዲሰራ በመጠየቅ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

