ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ዘርፍ መካከለኛ አመራሮች ለተከታታይ ስምንት ሳምንታት ሲሰጥ የቆየው «ስሜታዊ ብልህነት ለውጤታማ አመራር» (Emotional Intelligence for Effective Leadership) በሚል ርዕስ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ግንቦት 14/2018 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሥልጠናው ቀደም ሲል በተቋሙ ውስጥ በተማሪነት፣ በመምህርነት ባገለገሉት በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ (አሜሪካ) የ EmoIntel Leaders Corner ዋና ሥራ አስፈጻሚ (CEO) እና ዓለም አቀፍ የእውቅና ማረጋገጫ ያላቸው የEQ አሰልጣኝ በሆኑት ኢ/ር ዮናስ ገብረጻዲቅ ሐጎስ የተሰጠ ሲሆን ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለውድ ተቋማቸው ለማካፈል ባደረጉት የበጎ ፈቃድ ተነሳሽነት የተዘጋጀ ነው።

የሥልጠናው አቅራቢ ኢ/ር ዮናስ ገብረጻዲቅ እንደገለጹት ዘላቂ ተቋማዊ ዕድገትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው በአመራሩ ሁለንተናዊ ብቃት ላይ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመምራት ቴክኒካዊ ዕውቀት ብቻውን በቂ አለመሆኑን የጠቆሙት አሰልጣኙ፤ ከፍተኛ የስሜት ቁጥጥር፣ ሌሎችን የመረዳት አቅም (Empathy) እና የተሳለጠ የግንኙነት አስተዳደር ክህሎት የወቅቱን መሪዎች አቅም በቀጥታ ለመገንባት እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው ሥልጠናው እነዚህን መሠረታዊ ቁልፍ ብቃቶች ማዕከል ባደረጉ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ተዋቅሮ መሰጠቱን አብራርተዋል።

የአመራር ባህሪ ለውጥ ቀጣይነት ያለው ልምምድ ስለሚያስፈልገው፣ በሥልጠናው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት «ራስን ማወቅ» ላይ በማተኮር የአመራር ድክመቶችን (Blind Spots) መለየትና የግል ስሜት ቀስቃሽ ነገሮችን (Triggers) መረዳት ላይ ሰፊ ትንተና ተደርጓል። በሦስተኛውና አራተኛው ሳምንት «ራስን መቆጣጠር» በሚል መሪ ሐሳብ ጫና የበዛባቸውን አካዳሚያዊ አካባቢዎች በአግባቡ መምራትና በአስተዳደራዊ ቀውሶች ወቅት መረጋጋትን ስለመጠበቅ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ በአምስተኛውና ስድስተኛው ሳምንት ደግሞ «ማህበራዊ ግንዛቤን» በማሳደግ ንቁ የማዳመጥ ክህሎትን ማዳበር እንዲሁም የመምህራን፣ የሠራተኞችና የተማሪዎችን ፍላጎት በጥልቀት መረዳት አተኩሮ ተሰጥቷል። የመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት ደግሞ በ«ግንኙነት አስተዳደር» ላይ ያተኮሩ የነበሩ ሲሆን ገንቢ የሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የቡድን ተነሳሽነትን መፍጠርና የረጅም ጊዜ ተቋማዊ እምነትን መገንባት በሚሉ ወሳኝ ይዘቶች ላይ በስፋት ተሠርቷል።

ዶ/ር አዳነች ዘመዴ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዓለም አቀፋዊነትና ትብብር አስተባባሪ ለዩኒቨርሲቲያችን መካከለኛ አመራሮች ይህ የ«ስሜታዊ ብልህነት ለውጤታማ አመራር» ሥልጠና እንዲሰጥ ለማድረግ፣ በአሜሪካ አገር ከሚገኘው የ EmoIntel Leaders Corner ዋና ሥራ አስፈጻሚ (CEO) እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የEQ አሰልጣኝ ኢ/ር ዮናስ ገብረጻዲቅ ጋር የደብዳቤና የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ሥልጠናው በተሳካ ሁኔታ እንዲመቻች ሰፊ የቅንጅት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
 
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ካምላክነሽ ደሳለኝ በማጠቃለያው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሥልጠናው ለአስተዳደር ዘርፍ መካከለኛ አመራሮች የተሰጠ ሲሆን፣ የሥልጠናው ዋና ዓላማ የአስተዳደር ዘርፉን አሠራር በዘመናዊ መንገድ በመቅረጽ፣ ዩኒቨርሲቲው ለውስጥና ለውጭ ደንበኞቹ የላቀና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም ተፈላጊ፣ ተመራጭና ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።

ኢ/ር ዮናስ ገብረጻድቅ ለሥልጠናው ስኬት ከፍተኛ ሙያዊ ክትትልና አስተዳደራዊ ድጋፍ ላደረጉት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከሎጂስቲክስ አንጻር እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የመሠረተ ልማት እና የኢንተርኔት ቅንጅት ያለምንም እንከን ላቀረበው ለ IUC ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ለዩኒቨርሲቲው አይሲቲ ባለሙያዎች፣ ለዓለም አቀፋዊነትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊ የነበሩት አመራሮች በሰጡት አስተያየት፤ ሥልጠናው ያለፉ የአመራር ድክመቶቻቸውንና ስህተቶቻቸውን በግልጽ የፈተሹበት እንዲሁም ለወደፊቱ የተሻለ የመሪነት ግንዛቤ የጨበጡበት መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ማንኛውንም ተቋማዊ ውሳኔ ከራስ አመለካከትና አንግል ብቻ ተነሥቶ በችኮላ ከመወሰን ይልቅ፤ ከተቀመጡ መመሪያዎች፣ ደንቦችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት አንጻር በማገናዘብና በውጤታማ ተግባቦት መወሰን እንደሚገባ ትልቅ ትምህርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ኢ/ር ዮናስ ገብረጻዲቅ የመጀመሪያው ዙር ሰልጣኞች ባሳዩት ከፍተኛ ፍላጎትና የአመለካከት ተፅዕኖ ምክንያት፣ ድርጅታቸው EmoIntel Leaders Corner በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘላቂ የሙያ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወደፊትም ተጨማሪ የስልጠና ዙሮችን ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን በይፋ አረጋግጠዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት