አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት (GIZ) እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በደቡብ ኦሞ - ቱርካና ድንበር ተሻጋሪ ቀጠና የሚታዩ የፍልሰት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የግጭት ቅነሳ እና የሰዎች ዝውውር ችግሮች ላይ ያተኮረ የምርምር ማረጋገጫ (Validation) ወርክሾፕ ሰኔ 11 ቀን 2018 . በኃይሌ ሪዞርት አካሂዷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡


 
በተለይም በጂ አይ ዜድ (GIZ) በሚመራው "የተሻሻለ የፍልሰት አስተዳደር" (Better Migration Management - BMM) ፕሮግራም አማካኝነት በተከናወነው በዚህ ከፍተኛ መድረክ ላይ፤ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

 

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር / ቶሌራ ሴዳ በወቅቱ እንደገለጹት የውይይቱ መድረኩ በድንበር ተሻጋሪ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ በምርምር የተደገፈ መፍትሔ፣ የተቀናጀ ትብብር እና ጠንካራ አጋርነትን እንደሚጠይቅ አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከአገር ውስጥና ከውጭ አጋሮች ጋር በመሆን በበርካታ ዘርፎች ስኬታማ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን አስታውሰው፣ ይህ ወርክሾፕ የፖሊሲ ሃሳቦችን በማመንጨት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

 

የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አብርሃም ክንፈ በበኩላቸው የመድረኩ ዋና ዓላማ የጥናቱን ግኝቶችና ምክረ-ሀሳቦች ማረጋገጥ (validate ማድረግ) መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ወርክሾፑ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን፣ ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የሲቪል ማኅበራትንና የልማት አጋሮችን በአንድነት ያሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣ ፍልሰት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና መፈናቀል መካከል ያለውን ውስብስብ ትስስር ለመፈተሽ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

የተሳታፊዎች ልምድና እውቀት የጥናቱን ግኝቶች ይበልጥ ለማበልጸግና በእነዚህ ችግሮች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሔዎችን ለመቅረጽ እጅግ ጠቃሚ ነው ሲሉም አቶ አብርሃም አክለዋል፡፡

 

ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት (GIZ) የመጡት /ሪት እስራኤል ደጉ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የአካባቢ መራቆትና የኑሮ ዕድሎች መጥበብ ምክንያት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ተግዳሮት የአካባቢውን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ስደተኞችን፣ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎችን እና ተፈናቃዮችን ጭምር የሚጎዳ መሆኑን አብራርተዋል። ይህ የቢኤምኤም (BMM) ጥናት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭትና በሰዎች መንቀሳቀስ መካከል ያለውን ትስስር በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት፣ የመከላከያ ሥርዓቶችን ለማጠናከር እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማስገኘት እንደሚያግዝም /ሪት እስራኤል ገልጸዋል።

 

 

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ተመራማሪ / ሳም ፊዮናህ በበኩላቸው የወርክሾፑን ዋና ዓላማና አስፈላጊነት ሲያብራሩ፤ መድረኩ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን በአንድነት በማገናኘት በደቡብ ኦሞ-ቱርካና ቀጠና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ግጭቶችን፣ ፍልሰትን፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ መፈናቀልን እና ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮችን በተመለከተ ያሉ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ በስፋት ለመወያየት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

 

"የተሳታፊዎች ልምድ፣ እውቀትና የምሁራን ጠቃሚ አስተያየቶች የምርምር ግኝቶቹን ይበልጥ ለማበልጸግና በእነዚህ ችግሮች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ቀጣይ ሥራዎችን (practical interventions) ለመቅረጽ እጅግ የላቀ ሚና ይጫወታል" ሲሉም / ሳም አክለዋል፡፡

 

በዕለቱ / ሳም ፊዮናህ ከሌላው የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ከአቶ ዳኛቸው ወርቁ ጋር በመሆን ያጠኑትን የምርምር ሥራ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ሰፊ አስተያየትና ጠቃሚ ግብዓቶች ተሰጥቶበታል።

 

በዕለቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና አጋር ኢትዮጵያ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ የሚያስችል የትብብር መግባቢያ ስምምነት (MoU) የተፈራረሙ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በአካባቢው የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ የጥበቃ አገልግሎቶችንና የምርምር ሥራዎችን ለማጠናከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል። በዚህም መሠረት ሁለቱ ተቋማት በትብብር፣ በዕውቀት ልውውጥ ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማጠናከር የተስማሙ ሲሆን፣ በተለይም በሙያ ክህሎት ልማት፣ በሥራ ፈጠራ፣ በሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ እንዲሁም በፍልሰትና መፈናቀል ዙሪያ የጋራ ምርምሮችን በማከናወን በጋራ እንደሚሰሩ ታውቋል።

 

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/ 

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት