በአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት 22ኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የውኃ ሀብት ልማት ሲምፖዚየም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ 7 - 8/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በኢፌዴሪ ውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የውሀ ሀብት አጠቃቀም እና የኢነርጂ ፖሊሲ በማውጣት የተቀናጀ የውኃ አስተዳደር በማስፈን የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሸን ዘርፍን ለማጠናከር ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከ80-90 ከመቶ ከውኃ ኃይል የሚገኝ ኢነርጂ መኖሩን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ለ71 ሚሊዬን ያህል የሀገራችን ሕዝብ ንጽሕናው የተጠበቀ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ውኃ ቁጥጥር ኢንስቲትዩት (International Water Management Institute/IWMI) የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶ/ር አብዱልከሪም ሰኢድ በቁልፍ መልእክታቸው የውኃ አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን እና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የከተሞች መስፋፋት ፈታኝ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ጥራት ያለው መረጃ ቢያስፈልግም በአፍሪካ ያለው የተፋሰስ መረጃ የጥቂት ወንዞች ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር አብዱልከሪም ሳይንስና ምርምር በገሀዱ ዓለም ያለውን የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት ወሳኝ በመሆኑ የዕውቀት አድማስን በማስፋት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተሻለ ሁኔታ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ መሰል ሲምፖዚየሞችን በማዘጋጀት በዩኒቨርሲቲው፣ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ማዕከላት የተሠሩ ምርምሮች እንደሚቀርቡ አስታውሰው በሲምፖዚየሙ ለሀገር ልማትና እድገት የሚውሉና ለፖሊሲ አውጪዎች አቅጣጫ የሚጠቁሙ የምርምር ሃሳቦች እንደሚንሸራሸሩ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በበኩላቸው ዘላቂ ልማትን ስናስብ ለመጭው ትውልድ ጭምር አቅዶ መሥራትን እንደሚጠይቅ ተናግረው ይህንን ለማሳካት በየዓመቱ የውኃ ሀብትን በዘላቂነት ለመጠቀም በሚያስችሉ ምርምሮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ለማካሄድ ሲምፖዚየም ይዘጋጃል ብለዋል፡፡ በሲምፖዚየሙ ከቀረቡ 80 ወረቀቶች ከወቅታዊነትና ከችግር ፈቺነት አንጻር ተገምግመው 20 የምርምር ሥራዎች ተመርጠው 17ቱ በቃል እና ሦስቱ በፖስተር ገለጻ መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች መካከል አንዱ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመጡት ዶ/ር ተስፋለም አብርሃም ‹‹Towards Cooperation on the Three Large Dams on Transboundary Rivers in Ethiopia Achieving a win-win Balance between Upstream Hydro Power Generation and Downstream Water Demand under Climate Change›› በሚል ርእስ የቀረበው ነው፡፡ ጥናቱ በአባይ፣ ኦሞ እና ተከዜ ግድቦች ላይ የተሠራ ሲሆን በአካባቢው ያለውን የውኃ አጠቃቀም ከፍ ለማድረግና ኃይል የማመንጨት አቅምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ስምምነት የለም ያሉት ዶ/ር ተስፋለም በጥናታቸው በሀገራቱ መካከል የሚፈጠረውን ችግር በመቅረፍ እና በታችኛውና በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት መካከል መግባባትን በመፍጠር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን  ሊያመጣ የሚችል የመፍትሔ ሃሳብ መጠቆማቸውን ገልጸዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ መጨረሻ የማጠቃለያ መልዕክት ያስተላለፉት የምርምርና ማኅ/ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደክዮስ ሲምፖዚየሙ የውኃ ሀብት ዘላቂ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ መቀጠሉ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ እያደረገ ላለው የማይቋረጥ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ለሲምፖዚየሙ ዝግጅት አጋር የሆኑ ተቋማትንና በዕለቱ ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉ እንግዶችን በልዩ ሁኔታ ያመሰገኑት ም/ፕሬዝደንቱ ለተሳታፊዎች የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀትም አበርክተዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ የኢፌዴሪ ውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ በዓለም ውኃ ቁጥጥር ኢንስቲትዩት የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶ/ር አብዱልከሪም ሰኢድ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት