የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ጀርመን ሀገር ከሚገኘው ሳሃይ ሶላር አስሶሴሽን ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ቆጎታ ወረዳ በቆጎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 3.5 ሚሊየን ብር ያሰራው 5 ኪሎ ዋት የሚያመንጭ የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች በተገኙበት የካቲት 5/2018 ዓ/ም ተመርቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ዘርፍ ውጤታማነትና የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የገጠር ትምህርት ቤቶች የመብራት ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ የሚገኘውን ሥራ ለአብነት ያነሱት ፕሬዝደንቱ በዛሬው ዕለት ተመርቆ አገልግሎት የጀመረው የሶላር ኃይል አቅርቦት የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በእጅጉ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው በአከባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በኢንፎርሜሽን ከሚዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ አግልግሎት ያቆሙ ቤተ-ሙከራዎችን በአግባቡ አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማደረግ፣ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠትና በሌሎች መስኮች  እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባቋቋመው STEM ማዕከል ከ7-9 ያሉ የተመረጡ ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲው በማምጣት በተቋሙ በሚገኙ ቤተ-ሙከራዎች በሳይንስ ትምህርቶች የተግባር ልምምድ እንዲያደረጉ በማድረግ ለተማሪዎች ውጤታማት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ተክሉ በቆጎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተዘረጋው የሶላር መሠረተ ልማት 5 ኪሎ ዋት ኃይል  ማመንጨት የሚችል በመሆኑ ከትምህርት ቤቱ ባሻገር ለአከባቢው ማኅበረሰብ ጭምር አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ባለፈው ዓመት በጋሞ ዞን ዲታ ወረዳ በጎዛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ተመሳሳይ ሥራ መከናወኑን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ  ዩኒቨርሲቲው ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በዘርፉ ባከናወነው ሥራ በጋሞና ጎፋ ዞኖች የሚገኙ 20 ትምህርት ቤቶችንና 28 ጤና ጣቢያዎችን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ የቆየ መሆኑን ገልጸው ማኅበረሰቡም የተሰሩ መሠረተ ልማቶችን ጥንቃቄ መያዝ እንደሚገባው  አደራ ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ያሊሾ ግርማ ዩኒቨርስቲው በታዳሽ ኃይል ዙሪያ ሥራዎችን መስራት የጀመረው በ2001 ዓ/ም መሆኑን ገልጸው በዚህም በርካታ ከዋናው መስመር የራቁ የገጠር ትምህርት ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ የመብራት ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በእጅጉ አሻሽሏል ያሉት ዶ/ር ያሊሾ  የምርምር ማዕከሉ በቀጣይ ጊዜያትም በዘርፉ የጀመራቸውን የምርምር፣ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አውስተዋል፡፡

የቆጎታ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ዕጩ ዶ/ር ዳጌታ ዳለ ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት እጅግ ወሳኝና ከድህነት መውጫ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ ረገድ እያከናወነ የሚገኘው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ዩኒቨርሲቲው በገጠር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ እየሰራ የሚገኘው ተግባር በእጅጉ የሚያስመሰግነው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቆጎታ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥሞና ጭዳ በትምህርት ቤቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለመኖር የመማር ማስተማር ስራ ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸው አሁን ላይ ት/ቤቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑ የነበረውን ክፍተት በመሙላት በተለይ የትምህርቱን ሥራ በተግባር የተደገፈ ለማድረግ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት