አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 2,544 ተማሪዎች ሰኔ 27/2016 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) እንደገለጹት የምርምር ዩኒቨርሲቲነት ተልእኮን የተቀበለው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ በ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስመረቅ የጀመረ ሲሆን የዛሬዎቹን ጨምሮ 43 ተማሪዎችን በ3ኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ3ኛ ዲግሪ የማስተማርና የማስመረቅ አቅሙን እያሳደገ መሄዱ ተልእኮውን እንዲወጣ እንደሚረዳው እንዲሁም የራሱንና የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ተመራማሪዎችን አቅምና የትምህርት ደረጃ ለማሳደግ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን አስጠብቆ በርካታ ዜጎችን ለሀገር ለማፍራት የማስተማሪያና የምርምር ቤተ ሙከራዎችና ሠርቶ ማሳያዎች ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ያስገነባውና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምናና ጤና ዘርፉን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ የዕለቱ ምሩቃን ሀገር አቀፉን የመውጫ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ያመጡ መሆኑንና ቀሪዎቹ በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ በድጋሚ ፈተናውን እንደሚወስዱ ጠቅሰው ተማሪዎች ያለመሰልቸትና በጠንካራ መንፈስ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) መንግሥት ለትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና በዚህም ከ1.7 ሚሊየን በላይ ዜጎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ትምህርት የአንድን ማኅበረሰብ ሕይወት ከመቀየር አኳያ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሣሪያ በመሆኑ ምሩቃን ተገቢውን ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ዝግጅት በማድረግ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ ዕውቀታቸውን ለሀገር በሚጠቅም መልኩ እንዲያውሉ ዶ/ር ኤባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን (አሉምናይ) ማኅበር ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ባይነሳኝ ለምሩቃን ባስተላለፈችው መልእክት ምሩቃን በብርቱ ጥረትና ድካም ለዚህች ቀን በመድረሳቸው የተሰማትን ደስታ ገልጻ ካሰቡበት ግብ ለመድረስና ህልምን ለማሳካት ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ከሚሰጠው ዕውቀት በላይ የራስ ጥረትና ከነባራዊው ዓለም የሚገኙ የሕይወት ልምዶች ወሳኝ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡ ምሩቃን ከዛሬ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን (አልሙናይ) በመሆናቸው በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰዊ ገጾች አማካኝነት ፎርም በመሙላት የማኅበሩ አባል እንዲሆኑም ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ጥሪ አቅርባለች፡፡
በዕለቱ በኢኮኖሚክስ፣ ማኔጅመንት እና አካውንቲንግ የትምህርት መስኮች ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል ሦስቱን በውጤታቸውን መሠረት ዓባይ ባንክ የሥራ ዕድል እንደሚሰጣቸው እንዲሁም የግል ሥራ ለመጀመር ለምትፈልግ አንዲት ሴት ተመራቂ የቢዝነስ ዕቅዷን በማቅረብ አስፈላጊውን እገዛ ከባንኩ እንደምታገኝ የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠ በምረቃ መድረኩ ቃል ገብተዋል፡፡
ከተመራቂዎቹ መካከል ተማሪ ሳሙኤል ሰይፉ 3.9፣ መኳንንት በየነ 3.91፣ ሀሚድ ብርሃኑ 3.91፣ ዮሐንስ በሐሩ 4.00፣ አዲሱ ብርሃኑ 3.91፣ አብሪሁ ብርሃነ 3.97፣ ብርቱካን ወርቁ 3.86፣ ልደቱ ተስፋነህ 3.87 እና ኢያሱ ብርሃኑ 3.98 በማምጣት ከየኮሌጆች፣ ኢንስቲትዩቶችና ት/ቤቶች የላቀ ውጤት አስመዝግበው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ተማሪ መቅደስ ዳዊት 3.68፣ ማርታ ጸጋዬ 3.81፣ ማርታ ዳንኤል 3.83፣ ወርቅነሽ እንዳለ 3.88፣ አማረች ታደሰ 3.7፣ እጹብ መኩሪያ 3.9፣ ብርቱካን ወርቁ 3.86፣ የአብሥራ ነስሩ 3.64 እና መቅደላዊት ፈቃደ 3.92 በማምጣት ከሴት ተማሪዎች በልዩነት ተሸልመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በ2016 የትምህርት ዘመን 24,541 ተማሪዎችን ሲያስተምር የቆየ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 124 የቅድመ እና 24 የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች የውጭ ሀገር ስኮላርሺፕ ተማሪዎች እንዲሁም 26 የቅድመ እና 7 የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ካሉ ዓለም አቀፍ የስደተኛ ጣቢያዎች የመጡ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተማሪዎች ናቸው፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት