ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ እና ድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሐግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ሰኔ 14/2017 ዓ/ም አስመርቋል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዩኒቨርሲቲው በ38ኛ ዙር ምረቃው የሳውላ ካምፓስ ምሩቃንን ጨምሮ  በመጀመሪያ ዲግሪ 2,049፣ በማስተርስ 276 እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ 25 በድምሩ 2,350 ተማሪዎችን አስመርቋል ።

የሃይማኖት አባቶችና የጋሞ አባቶች ተመራቂ ተማሪዎች ለሀገር ለወገን የሚበጁ እንዲሆኑና በየሄዱበት ሁሉ መልካም እንዲገጥማቸው እንዲሁም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ጽኑ ሰላምን በመመኘት መርሐ ግብሩን በምርቃት እና መልካም ምኞት አስጀምረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል አንጋፋው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ከተመሠረተበት 1979 ዓ/ም ጀምሮ የመጀመሪያዎቹን 45 የዲፕሎማ ምሩቃን ጨምሮ 84,897 ምሩቃንን ለሀገር ማበርከቱን ገልጸዋል። የዛሬ ምሩቃን የትምህርት ዓለምን ብርቱ ትግል አልፈው ለዚህ ቀን በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ፕሬዝደንቱ ሙያዊ ዕውቀት ሁሌም መዘመንን የሚጠይቅ በመሆኑ ራሳቸውን ተወዳዳሪ በማድረግ ከዘመኑ ጋር መራመድና የሕዝብና የሀገር ኃላፊነትን ለመወጣት መትጋት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ ሞሩቃን በዩኒቨርሲቲው ባሳለፉት ጊዜ ላሳዩት መልካም ምግባርና ሰላማዊ ቆይታ አመስግነው በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ይህን መልካም አርአያነት እንዲያስቀጥሉ አደራ ብለዋል።

የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል ዶ/ር ደምሴ አድማሱ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በቁጥር ብዙ ምሩቃንን ብቻ ሳይሆን ጥራት ያላቸው፣ ችግር ፈቺ እና ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያራምዱ ምሁራንን ማፍራት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲያችን በመውጫ ፈተና የሚያሳልፋቸው ተማሪዎች ቁጥር የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ዶ/ር ደምሴ ለምሩቃን ባስተላለፉት መልእክትና የሥራ መመሪያ ይህ ቀን የትምህርት ዓለም ስኬትና የግል እድገት የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረው ምሩቃን ሀገሪቱም ሆነ ማኅበረሰቡ ከእናንተ የሚጠብቀውን ለማበርከት ሃሳብን በማመንጨት ወደ ተግባር የምትለውጡ ሥራ ፈጣሪዎች ልትሆኑ ይገባል ብለዋል። መጪው ጊዜ ዕውቀትን በክሂሎት በመደገፍ እንዲሁም በሥነ ምግባርና በማኅበራዊ ሕይወት በማደግ በትሕትና ሀገርን የሚያገለግሉበት እንዲሆንም አሳስበዋል። 

የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን (አሉምናይ) ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ የደረሱ እና ትልልቅ ተቋማትና ፕሮጀክቶችን የሚመሩ መሆኑ የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል። የዛሬ ሞሩቃንም ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ትልቅ ሥራ ላይ እንደምናገኛችሁ ተስፋ አለን ያሉት አቶ ኤርሚያስ በደረሳችሁበት ሁሉ የዩኒቨርሲቲው አምባሳደሮች ናችሁ ብለዋል።  ምሩቃን አብሮነታቸውን በማስቀጠል በጋራ ለመሥራት አሉምናይ ማኅበሩን እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ከየኮሌጁና ት/ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት እና የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ለወጡ የወርቅ ሜዳሊያ ተበርክቷል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ